Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በናይጄሪያ ታዋቂ የሆነው ድምፃዊ ዴቪድ አዴሌኬ ወይንም ዳቪዶ በማህበራዊ ሚዲያ በሰጠው ፖለቲካዊ አስተያየት ኢትዮጵያ ወይንም ሩዋንዳ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ይታሰር እንደበር የፕሬዝደንት ቦላ ቲኒቡ የሚዲያ አማካሪ ገለፁ፡፡ የናይጄሪያው ፕሬዝደንት የሚዲያ ከፍተኛ አማካሪው ቴሚቶፔ እጃዬ ይህንን የተናገሩት በአገሪቱ ኦሱን ግዛት በተካሄደው ምርጫ ገዢው ፓርቲ መሸነፉን ተከትሎ የድምፃዊው ሚና ምን እንደነበር ሲያብራሩ ነው፡፡

በግዛቱ የተደረገውን ምርጫ ያሸነፉት የዳቪዶ አጎት የሆኑት አዴሞላ አዴሌኬ ሲሆኑ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ድምፃዊው በማህበራዊ ሚዲያ ድጋፍ ሲሰጣቸው እንደነበር አውስተዋል፡፡ አማካሪው ሲናገሩ ‹‹ዳቪዶ በምርጫው ወቅት ገለልተኛ የፖለቲካ አስተያየት አልሰጠም፡፡ ለአጎቱ በንቃት ቅስቀሳ ሲያደርግ ነበር፡፡ በትዊተርና በማህበራዊ ሚዲያዎቹ በሙሉ የሚፅፋቸው ገለልተኛ ያልሆኑና አጎቱ እንደያሸንፉ ያለውን ፍላጎት የሚገልፁ መሆናቸው ግልፅ ነበር›› ካሉ በኋላ ድምፃዊው በናይጄሪያ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመናገር ነፃነት እንዳለው ገልፀው አንዳንድ ፅሁፎቹ ግን በህግ ያስጠይቁት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ጨምረውም ‹‹ዳቪዶ ከተናገረው ውስጥ 99 ፐርሰንቱ በብዙ አገራት ውስጥ የማይደፈር ነበር፡፡ ምክንያቱም እርምጃ ይወሰድበታል›› ብለዋል፡፡ የፕሬዝደንቱ አማካሪ በማስከተልም ለድምፃዊው ባስተላለፉት መልእክት ‹‹ዳቪዶ ኢትዮጵያ ወይንም ሩዋንዳ ብትሆን ትታሰር ነበር›› ማለታቸውን ሰሀራ ሪፖርተርስ ዘግቧል፡፡

1 month ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.