Logo
EBC
የታሪካዊው ምክክር ስኬት፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተጣለ መሰረት
******************

ኢትዮጵያ በታሪኳ አዳዲስ ምዕራፎችን በመክፈት የውይይትና የሰላም ባህልን በማጎልበት ረገድ ታሪክ የሚዘግበው ትልቅ እመርታ እያስመዘገበች ትገኛለች።

ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በጥይት ሳይሆን በውይይት እንዲሁም በመደማመጥ ባህል መፍታት እንደምትችል በተግባር ያረጋገጠችው ኢትዮጵያ ከተግዳሮቶች ወደ ብሩህ የተስፋ መንገድ በመሸጋገር ላይ ትገኛለች።

ዜጎቿም ካለፈው የታሪክ አጋጣሚዎች በቂ ትምህርት በመውሰድ በላቀ ጥንካሬ የምክክር ስኬትን ያበሰሩ ሲሆን ይህም ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ የተረጋጋች ነፃና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት ቁልፍ መሠረት ጥሏል።

ግጭትና ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጡ የተገነዘቡና ከመላ የሀገሪቱ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች እንዲሁም ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች የግል ጉዳዮቻቸውን ወደ ጎን በመተው በአዲስ አበባ በተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ በንቃት ተሳትፈዋል።

እነዚህ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ የተወከሉ ተሳፊዎች ላለፉት 46 ቀናት አካታች በሆነ መልኩ በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ያደረጉት ሁሉን አቀፍ ውይይት የ130 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ድምፅ በግልጽ ያንጸባረቀ ሆኗል።

ተመካካሪዎቹ የመተሳሰብና የመከባበር መንፈስ አንዱ የሌላውን ሀሳብ በማዳመጥ ሀገራዊ አንድነትን አጠናክረዋል።

ሂደቱን ለማስተጓጎልና ውዝግብ ለመፍጠር ከሀሰተኛ መረጃዎች ማሰራጨት ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም የምክክር ኮሚሽኑ ተቋማዊ ገለልተኛነቱን በመጠበቅና ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኑን በማስመስከር ኢትዮጵያና ህዝቦቿ አሸናፊ እንዲሆኑ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ይህንን ሀገራዊ ምክክር በስኬት ማጠናቀቋና ማሸነፏ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። በቅድሚያ ታሪካዊ ስብራቶችን በመጠገንና ዘላቂ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር የፖለቲካ ከባቢው እንዲረጋጋ ያደርጋል።

ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ ደግሞ የልማት እንቅስቃሴዎች ፍጥነታቸው የሚጨምር ሲሆን ማህበረሰቡ ያለምንም ስጋት በልማት ላይ እንዲያተኩር እድል ይፈጥራል።

በተጨማሪም ከማህበረሰቡ እውቀትና ተሞክሮ በመነሳት የተሰበሰቡት ውሳኔዎች የወደፊት የፖሊሲና የልማት አቅጣጫዎች የህዝቡን ፍላጎት በቀጥታ እንዲያንፀባርቁ ያስችላሉ።

ከሁሉም በላይ የሴቶችና የወጣቶችን ተሳትፎ በማስፋት የነገን ትውልድ እጣ ፈንታ በጋራ ለመቀረፅና ጠንካራ ሀገር ለማሸጋገር መሰረት የጣለ ሲሆን ይህ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት የመፍታት አቅም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የቀጠናው ሀገራት ትልቅ አርአያና አዲስ ብሩህ ተስፋ የሚፈንጥቅ ነው።

በኢንትሀድ አብራር
#ebc #ethiopia #nationaldialogue #ethiopiapeace #nationalconsultation

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.