Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የአሜሪካ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) መክፈል ከነበረበት በቢሊዮኖች ከሚቆጠር ውዝፍ እዳ ውስጥ 850 ሚሊዮን ዶላሩን ለመክፈል ማቀዱን ለሀገሪቱ ኮንግረስ አሳውቋል። ይህ ክፍያ የትራምፕ አስተዳደር የተመድ ዋነኛ የገንዘብ ደጋፊነቱን ለመቀጠል ተቋሙ ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያ እንዲደረግ ከጠየቀ ወዲህ የሚፈጽመው ከፍተኛው ክፍያ መሆኑ ተነግሯል።

አሶሼትድ ፕሬስ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ካቀደው ጠቅላላ ክፍያ ውስጥ 725 ሚሊዮን ዶላሩ የተመድን መደበኛ በጀት ለመደገፍ የሚውል ነው። ቀሪው 125 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በሄይቲ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለሚካሄደው የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ የሚሰጥ ይሆናል።

እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ፣ አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነቷ ጋር ተያይዞ ያልከፈለችው ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ውዝፍ እዳ አለባት። ከዚህ ውስጥ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነው ለመደበኛ በጀት ሲሆን፣ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ደግሞ ለሰላም አስከባሪ ስራዎች መከፈል የነበረበት ነው።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ድርጅቱ የፋይናንስ አሰራሩን ካልቀየረ ወይም ሁሉም 193 አባል ሀገራት ክፍያቸውን በወቅቱ ካልፈጸሙ ተቋሙ አፋጣኝ የሆነ የገንዘብ ቀውስ አደጋ እንደተጋረጠበት በቅርቡ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ይህ በተለይም ለአሜሪካ የተላለፈ መልዕክት እንደነበር ሲገለጽ፣ የትራምፕ አስተዳደርም ይህንን ተከትሎ ባለፈው የካቲት ወር ላይ የ160 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ፈጽሞ ነበር።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.