Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ዛሬ ሰኞ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፣ የኤርትራ ሉዓላዊነትም ሆነ የማንኛውም አፍሪካዊት ሀገር ሉዓላዊነት ለድርድር እንደማይቀርብ አሳስቧል። ዘ-ሐበሻ የተመለከተው ይህ መግለጫ በዋናነት "ዶይቼ ቬለ" እና "ፎሪን ፖሊሲ" መጽሔት በቀንዱ የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ የኤርትራን ሚና አስመልክተው ላወጧቸው ጽሑፎች የተሰጠ ምላሽ ነው። ኤምባሲው እነዚህ ሚዲያዎች የሀገሪቱን ታሪክ እያጣመሙ፣ ኢትዮጵያ ወደብ ለማግኘት የምታደርገውን የሉዓላዊነት ጥያቄ ህጋዊ ለማስመሰል ሞክረዋል በማለት ወቅሷል።

መግለጫው የንግድ ወደብ ፍላጎት እና የሌላን ሀገር የባህር ዳርቻ ወይም መሬት ሉዓላዊነት የመፈለግ ጉዳይ ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥቷል። የኢኮኖሚ ፍላጎት፣ የህዝብ ብዛት ወይም የጂኦግራፊ አቀማመጥ ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ለመጣስ እና የሉዓላዊነት ጥያቄ ለማንሳት ህጋዊ ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ አስቀምጧል። የባህር በር አልባ የሆኑ (Landlocked) ሀገራት ግዛት ሳይጠይቁ በስምምነት የጎረቤቶቻቸውን ወደብ እንደሚጠቀሙ ያነሳው መግለጫው፣ የንግድ ፍላጎት የትብብር እንጂ የመሬት ባለቤትነት መብትን እንደማያስገኝ አብራርቷል።

ሚዲያዎቹ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንደተገነጠለችና አዲስ አበባን ያለ የባህር በር እንዳስቀረች አድርገው ማቅረባቸውን የኮነነው ኤምባሲው፣ ይህ ድርጊት አሁን ላይ ለሚነሱ የድንበር ጥያቄዎች ሽፋን የሚሰጥ የታሪክ ስህተት መሆኑን አስገንዝቧል። ኤርትራ በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ወቅት እ.ኤ.አ. በ1890 የራሷን ዘመናዊ ድንበር ያበጀች ሀገር እንደሆነችና በ1993 ዓ.ም. በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ 99.8 በመቶ በሚሆነው ድምፅ ነፃነቷን ማረጋገጧን አስታውሷል። በተጨማሪም የኤርትራ እና ኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ እልባት ያላገኘ እንዳልሆነና፣ እ.ኤ.አ. በ2002 ዓ.ም. በተፈረመው የአልጀርሱ ስምምነት መሰረት በገለልተኛው የድንበር ኮሚሽን (EEBC) የመጨረሻ እና አስገዳጅ ውሳኔ ማግኘቱን መግለጫው በድጋሚ አረጋግጧል።

ከዚህም ባሻገር ኤርትራ ከግብፅ፣ ሶማሊያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና አሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የቀይ ባህር ሀገር በመሆኗ የሚመነጭ የደህንነት፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትብብር እንጂ፣ ሚዲያዎቹ እንዳሉት ኢትዮጵያን ለማግለል የታለመ ፕሮጀክት እንዳልሆነ ኤምባሲው አስተባብሏል። በተመሳሳይ የሀገሪቱን አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት እያመኑ በሌላ በኩል ደግሞ ስርአቱን "አምባገነን" እያሉ መፈረጅ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሀሳብ መሆኑን ተችቷል።

ኤርትራ የማንንም ሀገር መሬት እንደማትፈልግ እና ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤቶቿ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንደምትፈልግ መግለጫው አስታውቋል። የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ግን በማንኛውም የጂኦፖለቲካዊ ድርድር ውስጥ እንደማይገባ በጥብቅ አስገንዝቦ፤ ይህ ሉዓላዊነት ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያለው ህጋዊ መብት መሆኑን እና የማንኛውም አፍሪካዊት ሀገር ደህንነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትም በዚህ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በመግለጽ አጠናቋል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.