Logo
EBC
የቱሪዝም ካርታችን ሲቀየር፡ ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት
*******************

አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጀመረችው የኮሪደር ልማት እና የስማርት ሲቲ ግንባታ፤ የከተማዋን ውበት ከመቀየር ባለፈ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ አዲስ መነቃቃት እየፈጠረ ይገኛል።

የከተማ ቱሪዝም በዘመናችን እጅግ አዋጭ ከሚባሉ ዘርፎች አንዱ ሲሆን፣ አዲስ አበባም በዚህ ረገድ ያላትን እምቅ አቅም አሁን ላይ በተጨባጭ ማውጣት ጀምራለች።

በቅርቡ የተሠሩት ሰፊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መሄጃዎች እንዲሁም በምሽት ደማቅ ብርሃን የሚፈነጥቁ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች የከተማዋን የኑሮ ዘይቤ እያዘመኑት ነው። ይህ ደግሞ ቱሪዝም እንዲያንሰራራ ትልቅ መደላድል ፈጥሯል።

ጎብኚዎች ያለምንም የፀጥታ ስጋት በምሽት ወጥተው መዝናናት መቻላቸው ለመስተንግዶው ዘርፍ፣ ለካፌዎች፣ ለሬስቶራንቶች እና ለባህል ምሽት ቤቶች ተጨማሪ የገበያ ዕድል ይዞ መጥቷል።

አብዛኛውን ጊዜ የውጭ ቱሪስቶች አዲስ አበባን የሚጠቀሙባት ወደ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎች ለማለፍ እንደ መሸጋገሪያ ብቻ ነበር።

አሁን ግን እየተሠሩ ያሉት ማራኪ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የውኃ ትዕይንት እና አረንጓዴ ሥፍራዎች ጎብኚዎች በከተማዋ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲያራዝሙ አስገዳጅ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው። የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ መራዘሙ ደግሞ በቀጥታ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ የሚተረጎም ነው።

በመዲናዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስኬት ባለፉት አምስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በቱሪዝም ሴክተሩ የተከናወነው ሰፊ የመዋቅር ሽግግር አንድ አካል ነው።

ዘመናትን የተሻገረ ገናና ታሪክ እና ውብ ባህል እያለን፣ የቱሪዝም ዘርፋችን ከኢትዮጵያ ታላቅነት ጋር የማይመጣጠን ሆኖ የቆየበት ጊዜ አሁን አብቅቷል።

ተዘንግተው አቧራ የለበሱ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን አቧራቸው እየተራገፈ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲቀየሩ ያስቻሉ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ተግባራዊ ሆነዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎም ቱሪዝም ከአምስቱ ዐበይት የኢኮኖሚ አምዶች አንዱ ሆኖ ተቀርጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እይታ ግልጽ ነው፤ ኢትዮጵያ የታደለቻቸው የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ሀብቶች ሌሎች ሀገራት በሰው እጅ ከሠሯቸው መስህቦች በእጥፍ ይበልጣሉ።

ምድራችን ተፈጥሮ በራሷ የሠራቻት ታላቅ ፓርክ በመሆኗ፤፣ ይህን የተፈጥሮ ጸጋ በማልማት ለዓለም ማሳየት ቀዳሚ ተግባር ሆኗል።

በዚህም ኢትዮጵያን በርሃብ እና በችግር ሳይሆን በውበቷና በታሪኳ የማስተዋወቅ ራዕይ ከቃል አልፎ ተጨባጭ ተግባር በመሆን የቱሪዝም ካርታችንን ሙሉ በሙሉ እየቀየረው ይገኛል።

የዚህ ታላቅ ራዕይ ትልቅ ማሳያ ከሆኑ ሥራዎች መካከል የሸገር ፕሮጀክቶች ይገባቸዋል። በታላቁ ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የሚገኘው አንድነት ፓርክ፣ የአዲስ አበባን የወንዝ ዳርቻ ወደ ዘመናዊ መዝናኛነት የለወጠው የወዳጅነት ፓርክ እንዲሁም አቧራማ የነበረውን ስፍራ ወደ ሥነ ምህዳር ቱሪዝም ማዕከልነት የቀየረው እንጦጦ ፓርክ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።

በተጨማሪም የሳይንስ ሙዚየም ለቴክኖሎጂ ቱሪዝም በር ሲከፍት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ዓድዋን በጥበባዊ መልኩ በመግለጥ ጎብኚዎችን እየሳበ ይገኛል።

ከእንጦጦ እስከ ቀበና፣ የራስ መኮንን ድልድይ እንዲሁም የጊዮን አካባቢ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የኮሪደር ልማቱን አድማስ አስፍተውታል። ይህ የልማት ተሞክሮ በገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከመዲናዋ ወደ ክልሎች በመስፋት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ፈጥሯል።

በዚህም በጣና ሐይቅ ዳርቻ ታሪካዊውን ጎርጎራን፣ ተፈጥሮን በጠበቀ መልኩ ለኢኮ ቱሪዝም ያመቻቸውን ወንጪ-ደንዲን እንዲሁም የተፈጥሮ ውበትን ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ያጣመረውን ኮይሻን ማልማት ተችሏል።

የዱር አራዊትን በተለይም ዝሆኖችን ለመመልከት ምቹ የሆነው የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን ያልተነካ ፀጋ ለዓለም እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች ትልቁ ስኬት የቱሪስት መዳረሻዎችን ከመገንባት ባለፈ ያመጡት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ነው።

ቱሪዝም ለውጭ ቱሪስቶች ብቻ የተከለለ ያስመስል የነበረውን አስተሳሰብ ቀይሮ ዜጎች ኢትዮጵያን እንዲያውቁ በማድረግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ባህልን አሳድገዋል።

በአጠቃላይ ዘርፉ አመርቂ በሆነ መልኩ እያደገ መምጣቱ ለኢኮኖሚያችን ትልቅ አቅም አድርጎታል።

በበረከት ሽመልስ
#ethiopia #ebc #tourism #addisababa #smartcity #travelethiopia

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.