Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) መቼም በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የምትኖሩ ወገኖች ዛሬ ማለዳ በትራፊኩ መጨናነቅ እና መስተጓጎል የተነሳ 'ምን ተፈጥሮ ይሆን?' ብላችሁ መጠየቃችሁ አልቀረም። ምክንያቱ ግን እጅግ አስገራሚ፣ አልፎ ተርፎም ፈገግ የሚያሰኝ ሆኖ ተገኝቷል።

ዛሬ ማለዳ (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ትናንት) 1፡00 ሰዓት አካባቢ፣ በሰሜን ምዕራብ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ታሪካዊው የቴንሊታውን ሰፈር ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። በአንድ የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያ አቅራቢያ የተተወ አጠራጣሪ እቃ፣ የጸጥታ ኃይሎችን እግር በእሳት አስጠብቆ የጠዋቱን የተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰት ለሁለት ሰዓታት ያህል ሙሉ በሙሉ አስቁሞት አርፍዷል።

የአካባቢው የጸጥታ አካላት እና የዋሽንግተን ዲሲ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ይህንን "አጠራጣሪ እሽግ" እንደ ትልቅ የጸጥታ ስጋት በመቁጠር በአፋጣኝ ወደ ስፍራው አቀኑ። ዘ-ሐበሻ ያገኘው የፖሊስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ አንድ ግለሰብ ወደ ጣቢያው ጀርባ በመምጣት የኤሌክትሪክ ገመዶቹ ወደ ውጭ የወጡበትን ይህን እቃ ጥሎት መሄዱ ታውቋል። የገመዶቹ ወደ ውጭ መውጣት ደግሞ እቃው አደገኛ ፈንጂ ወይም ቦምብ ሊሆን ይችላል የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬን ፈጥሮ ነበር።

ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የቦምብ አምካኝ ባለሙያዎች እና ልዩ አፋሽ የፖሊስ ውሾች (K-9 Units) አካባቢውን አጥረው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ፍተሻቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ሆኖም ከከፍተኛ ጥንቃቄ እና ፍርሃት በኋላ፣ ይህ መላውን ሰፈር ያሸበረው እና መንገዶችን ያስዘጋው ቁሳቁስ ምንም ዓይነት አደጋ የማያስከትል "ሰማያዊ እና ጥቁር ቀለም ያለው ኤሌክትሮኒክ ተንቀሳቃሽ የሴክስ (የወሲብ) መጫወቻ" ሆኖ ተገኝቷል።

ፖሊስ እቃውን ከስፍራው በማንሳት የትራፊክ ፍሰቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ያደረገ ሲሆን፣ በክስተቱ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱ ተረጋግጧል። ጉዳዩን የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ዲፓርትመንት ተጨማሪ ምርመራ እያደረገበት ይገኛል። በርግጥም የዛሬው የዲሲ የትራፊክ መጨናነቅ ሰበብ፣ በነዋሪው ዘንድ ግርምትን የፈጠረና በፈገግታ የሚታወስ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.