Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ስፖርት) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለፊፋ ፕሬዝደንት ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ለፊፋ ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በሙሉ ድምፅ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑን ገለፀ፡፡ በኢንፋንቲኖ አመራር ላይ በመላው አለም ተቃውሞ እየተነሳ ባለበት በዚህ ወቅት ካፍ ተቃራኒ አቋም በማንፀባረቅ ፕሬዝደንቱን ደግፏል፡፡ ካፍ ይህንን አቋሙን ዛሬ ይፋ ያደረገው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ኢንፋንቲኖ በስልጣን ላይ የሚቆዩ ከሆነ በፊፋ ውድድሮች ራሱን እንደሚያገል ማስታወቁን ተከትሎ ነው፡፡ ለአህጉሪቱ እግር ኳስ እድገት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ያደነቀው ካፍ የፊፋ ፕሬዝደንትና ዋና ፀሀፊው ያቀረቡለትን ወቅታዊ ገለፃ እንደተቀበለው አስረድቷል፡፡

በዚህም በፊፋ ውስጥ ግልፅነት ያለው መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡ የካፍ ፕሬዝደንት ፓትሪስ ሞትሴፕ ሲናገሩ ‹‹ለእኛ ለአፍሪካዊያን በአስተዳደርና በፍትህ ሂደት ውስጥ ግልፅነት ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡

ስለዚህም ከመንግስቶቻችን፣ ከንግድ ድርጅቶችና ከሌሎችም ተቋማት ይህንን እንጠብቃለን፡፡›› ያሉ ሲሆን ካፍ እነዚህን መርሆዎች በማክበር ከፊፋ፣ ከአባል ማህበራትና ሌሎችም አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖችና የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላት ጋር መስራቱን እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውይይት አድርጎ በሙሉ ድምፅ ለኢንፋንቲኖ ድጋፍ ለመስጠት ውሳኔ እንደደረሰም አስታውቀዋል፡፡

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.