Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ኦገስት 1 ቀን በትግራይ ኃይሎች እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት (ENDF) መካከል ዳግም ያመረቀዘውን ግጭት ተከትሎ፣ የክልሉ ነዋሪዎች ለአዲስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አደጋ መጋለጣቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቀጠናዊ ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ ባወጡት መግለጫ፣ ማህበረሰቡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙበትን አሰቃቂ በደሎች ያለ ምንም ፍትህ እና ተጠያቂነት እያስተናገደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ አዲሱ የትጥቅ ግጭት ነዋሪዎቹን ወደ ከፋ አደጋ ውስጥ ጥሏቸዋል ብለዋል።

ቀጠናዊ ዳይሬክተሩ አክለውም ይህ በትግራይ ዳግም ያገረሸው ጦርነት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ቀጥሎ ከሚገኘው እና ተቋማቸው ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየመዘገበበት ካለው የትጥቅ ግጭት ጋር ሲደመር፣ ሀገሪቱ አፋጣኝ የሆነ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ምርመራ ዘዴዎችን ወደ ነበረበት መመለስ እንዳለባት አመላካች ነው ሲሉ አሳስበዋል። ከህዳር 2013 እስከ ህዳር 2015 ዓ.ም. በተካሄደው ጦርነት የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሊባሉ የሚችሉ ከባድ ጥሰቶች መመዝገባቸውን ያስታወሰው ተቋሙ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ታማኝ ምርመራ አለማድረግን እና የጥፋተኞችን የህግ ተጠያቂነት ማስፈን አለመቻልን እንደ መደበኛ አሰራር ሊቆጥረው አይገባም ሲል አስጠንቅቋል።

በመሆኑም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የፌደራል እና የትግራይ ባለስልጣናት የሲቪሎችን ጥበቃ ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መስፈርቶችን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል። ከዚህም ባሻገር ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ያለምንም እንቅፋት በቦታው ተገኝተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ሊፈቀድላቸው እንደሚገባ ተማጽኗል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ከሚገኙ ባለስልጣናት ጋር በአስቸኳይ በመነጋገር በግጭቱ ለተጎዱ የትግራይ አካባቢዎች የነጻ ሚዲያዎች እና የሰብዓዊ መብት ታዛቢዎች ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ተቋሙ ወትውቷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ይደረግ የነበረው ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ክትትል የተቋረጠው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን (ICHREE) እና የአፍሪካ የሰብዓዊ እና ህዝቦች መብት ኮሚሽን አጣሪ ቡድን የስራ ጊዜ ማብቃቱን ተከትሎ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም አቀፍ የተጠያቂነት ጥረቶችን ለመከላከል ሲጠቀምበት የነበረውን የሽግግር ፍትህ ሂደት እርግፍ አድርጎ ትቶታል ሲል መግለጫው ወቅሷል። በሌላ በኩል ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የትግራይ ባለስልጣናት ነጻ ሚዲያዎችን ከማፈን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በግዳጅ ወደ ጦርነት ከመመልመል እና የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ከመገደብ ጋር የተያያዙ አፋኝ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መመዝገባቸውን አምነስቲ አጋልጧል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.