Logo
Getu Temesgen
ከፍተኛ ግብር የሰበሰቡ ተሸለሙ
"...ምን ማለት ነው?"
(ሙሼ ሰሙ)
#ethiopia | "ከፍተኛ ግብር የሰበሰቡ ተሸለሙ" የሚል ዜና በስፋት እየተዘገበ ነው። ከፍተኛ ግብር ሰበሰቡ ማለት ምን ማለት ነው ?! አንጻሩስ ምንድን ነው ? በጀት ነው ? ኮታ ነው? ወይስ የትም ፍጪው ዲቄቱን አምጭው ነው ? ከበጀት በላይ ማትረፍ እንጂ ከበጀት በላይ ግብር መሰብሰብስ እንዴት ይቻላል? ይህ አዲስ ግኝት ነው?

በደሞዝ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ "ውጤታማ ሲሆን" ጉርሻ ( Bonus) ከመስጠትና ደሞዙን ከማሳደግ አልፎ ለተቋሙ አገልግሎት የሚውል ቢሆንም በየዓመቱ ተሽከርካሪ መለወጥ የትኛው መንግስታዊ አሰራርና ደንብ እንደሚፈቅድ የውጭ ኦዲተር መጠየቅ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል ?

ወደ ዋነኛ ጉዳዬ ልመለስ ።

እርግጥ ነው። ነጋዴ ንብረቱን ላለማጣትና ድርጅቱን ላለመዝጋት ሲል ጥሪቱንና አቅሙን አሟጦ እስኪጨርስና ቤቱ እስኪከረቸም ድረስ ከበጀትም ከኮታም በላይ እጥፍ ድርብ ግብር በማስከፈል ከበጀት በላይ ገንዘብ መሰብሰብ ይቻላል። ተችሏልም። ጥያቄው ግን እስከመቼ የሚለው ነው ?!

በዚህ መንገድ የመንግስት ገቢ አንድ ሺ ፐርሰንት ሊያድግና ሊመነደግ ይችላል። በኮታና በነሲብ ግብር የመሰብሰብ ዘመቻ በሂደት የነጋዴውን ገቢ እያዳከመና ትርፉን እያቀጨጨ ከመሄድ ውጭ ጤናማ የንግድ፣ የግብይይትና የግብር ስርዓት ሊፈጥር አይችልም። ንግድ ፈቃዱን በሰልፍ የሚመልሰውና ድብብቆሽ የሚጫወተው ነጋዴም ለዚህ ክስተት ሕያው ምስክር ነው። ለምን ቢባል ንግድ ለጽድቅ የሚሰራ ስራ አይደለም።

ለማንም ግልጽ እንደሚሆነው በጤናማ መንገድና በሕግ አግባብ የሚነግድ፣ የሚሰራና የሚያመርት ሰው (ካልከሰረ በስተቀር) ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ከትርፉ ጥሪት በመቋጠርና አቅሙን በማጎልበት ንግዱን በማስፋፋት፣ የስራ እድል መፍጠርና ወደ ሚቀጥለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ መደብ ( Economic Class) መሸጋገር መቻል አለበት።

ጤናማ የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግር፣ የንግድና የግብር ስርዓት መስተጋብር ማለት ይህው ብቻ ነው። ነጋዴውን አሟጦ በማስገበር ማቀጨጭና በሂደት ከገበያ እንዲወጣ ማድረግ የልማት፣ የእድገትና የምርታማነት እንቅፋት ከመሆን ባሻገር ሕገ ወጥነትና የጓሮ በር ድርድር እንዲስፋፋ በር መክፈት ብቻ ነው። በገሃዱ ዓለምም እየሆነ ያለውም ይህው ነው።

ጤናማ የግብር ስርዓት ንግድና ነጋዴው እንዲያብቡ አመቺ ሁኔታን በመፍጠር አምራቹን፣ ባለኢንዱስትሪውን፣ ቸርቻሪውን አከፋፋዩንና አስመጭውን በቁጥርም በአቅምም እንዲጎለብቱ በማገዝ ከሚፈጠረው ሰፊ የንግድ አቅምና ከሚሳለጠው የምርትና የግብይይት ስርዓት ከእያንዳንዱ ነጋዴ ላይ ተመጣጣኝ ግብር በመሰብሰብ በቅንጅት እንደ ሀገር ማደግ ይቻላል።

ይህ እውን መሆን የሚቻለው ነጋዴው በቂ ትርፍ አትርፎና ጥሪት ቋጥሮ የማምረት አቅሙን በማጎለብት ፣ ፋብሪካውንና ኢንዱስትሪውን በማሳድግ፣ የስራ እድልና አቅርቦትን በማስፋፋት እምቅ ሃይሉንና አቅሙን መጠቀም የማይገድበው፣ በተለይ ከገቢው ጋር የሚመጣጠን ግብር መገበር ሲችል ብቻ ነው።

በጥቅሉ በነሲብ፣ በጅምላና በኮታ የሚጣል ግብር የነጋዴውን ማህበረሰብ አቅም በማሟጠጥና ኪሱን በማራቆት በሂደት ተያይዞ መውደቅን እንጂ ተያይዞ ማደግን አያመጣም። "በነጻ ውድድር ገበያ የሚመራ" ነገር ግን ነጋዴ የሌለበት ወይም ሕገ ወጥነትና ጥገኛ ነጋዴ የተንሰራፋበት ሀገር መፍጠር ነው።

በተደጋጋሚ የሚነሳው የመንግስት ገቢና የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት አለመጣጣም መንስኤ ነጋዴው በቂ ግብር ባለመክፈሉ ብቻ ሳይሆን ሳይቀረጥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ሕገ ወጥ የገቢ ሸቀጥ መበራከት፣ ቫት የማይጎበኘው አቅርቦት መስፋፋት፣ መንግስት ማግኘት የሚገባው ነገር ግን በአስፈጻሚ አካላት ሙሰኝነት ባክኖ የሚቀር ገቢና በሕገ ወጥ ነጋዴዎችና በሙሰኞች መመሳጠር አየር ላይ ተበልቶ የሚቀረው ገቢ ከሚከፈለው ግብር እጅግ የላቀ መሆን ነው ። ( ማብቂያ የሌለው የገቢ የሚያቀጣጥሉ በገቢ አቅም በላይ ወጭ መልመድ፣ ብክነት፣ ዝርክርከነትና በአቅም አለመኖር ብቻውን ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ነው)

የመንግስት አስፈጻሚዎች ላይ የነሲብ አስገዳጅ ኮታ በመጣል ኮታቸውን ለመሟላት በየሱቁ፣ በየድርጅቱና በየፋብሪካው እየዞሩ ነጋዴውን ያልሸጠከውን ሸጠሃል። ያላመረትከውን አምርተሃል። ያላገኘውን ትርፍት አግኝተሃል በማለት አቅሉን በመሳት ወደ ሕገ ወጥነት እንዲያመራ ከመግፋት ይልቅ መንግስት የራሱን ጓዳ (የገቢዎችንና የጉምሩክን) አሰራር በመመርመርና በሙስና ተድበስብሶ አየር ላይ የሚቀረውን ግብር በመታደግ ገቢውን ማሳደግ፣ ወጭውን በመቆጣጠርና ቁጠባ በመለማመድ ገቢውን በእጥፍ ድርብ ማሳደግ ይችላል።

ነጋዴውንም ከመዋከብ፣ ከመሳደድ በመታደግ ተስፋ ከመቁረጥና የሙሰኞች መጫወቻ ከመሆን ተገላግሎ እፎይታ አግኝቶና ተረጋግቶ አዕምሮውን ለስራ፣ ጊዜውንና ጉልበቱን ለፈጠራና ለምርታማነት፣ ገንዘቡን ለእድገት እንዲጠቀም በማገዝ እየተፈራሩና እየተጠራጠሩ በጨለማ ከመዳከር ይልቅ የስራ ጊዜን ውጤታማ፣ የነጋዴውም ሆነ የሸማቹን ህይወት በተስፋ የተሞላና ብሩህ ማድረግ ይቻላል።

2 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.