Logo
EBC
የድኅረ-እውነት ፈተና፦ እውነት ዋጋ ባጣበት ዘመን ኢትዮጵያን ማዳን
**********************

በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዝብ አስተያየት አወቃቀር እና የፖለቲካ ንግግሮች ምኅዳር በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።

ለዚህም ዋነኛው ማሳያ፥ ተጨባጭ እና ሳይንሳዊ ሐቆች ለሕዝባዊ ውሳኔዎች መሠረት መሆን ሲገባቸው፣ ከእውነት ይልቅ ለሰዎች ስሜት እና ቀድሞ ለተነገሩ የግል እምነቶች የሚቀርቡ የማሳመን ሙከራዎች ከፍተኛውን ተፅዕኖ መፍጠራቸው ነው።

ምሁራን ይህን ጽንሰ-ሐሳብ "ድኅረ-እውነት" (post-truth) በማለት ይገልጹታል። ይህ ጽንሰ-ሐሳብ ሰዎች እውነትን ስለመቃወማቸው ሳይሆን፣ እውነት ራሱ ዋጋ ቢስ ወደሚሆንበት እና ከጉዳይ ወደማይቆጠርበት ደረጃ መድረሱን የሚያሳይ ነው።

ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ ይህን ሀሳብ ሲገልጽ፣ "ተጨባጭ የሆኑ ፍፁማዊ እውነታዎች የሉም፤ ያለው የሰው ልጅ የሥልጣን ፍላጎት የሚፈጥረው ትርጓሜ ብቻ ነው" ይላል።

ዛሬ ላይ እውነታን ከፈጠራ የመለየት አቅም ማጣት ማኅበረሰብን ወደ አጠቃላይ አምባገነናዊነት እና ትርምስ እየመራው ይገኛል።

የድኅረ-እውነት ፖለቲካ መፈጠር እና መስፋፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዴሞክራሲያዊ ተቋማት፣ በሕዝብ አመኔታ እና በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ውድቀቶችን አስከትሏል።

እ.አ.አ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ እና በእንግሊዝ የ‘ብሬግዚት' ውሳኔ ወቅት፣ ፖለቲከኞች የሕዝቡን የኢኮኖሚ ስጋት እና ብሔራዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት የምርጫውን ውጤት መለወጥ ችለዋል።

በተመሳሳይ እ.አ.አ በ2017 በሚያንማር በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ የጥላቻ እና የሐሰት ዘገባዎች በሀገሪቱ ለተፈጸመው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዋነኛ መንስኤ እንደነበሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለዚህ የመረጃ ሥነ-ምህዳር መዛባት ግንባር ቀደም መደላድል የፈጠሩት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፉ ያሉት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ናቸው።

የነዚህ መድረኮች የውሳኔ ሰጪ ስልተ-ቀመሮች (Algorithms) የተገነቡት የመረጃን እውነትነት ለማረጋገጥ ሳይሆን፣ የተጠቃሚዎችን ቀልብ በመሳብ መድረኩ ላይ ረጅም ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማድረግ ነው።

በዚህም የተነሳ ስሜት ቀስቃሽ፣ ጽንፈኛ እና አስደንጋጭ የሐሰት መረጃዎች በፍጥነት ይሰራጫሉ።

በተጨማሪም ተጠቃሚዎች የራሳቸውን አመለካከት ብቻ ከሚያስተጋቡ ሰዎች ጋር እንዲገናኙ በማድረግ፣ "Echo Chambers" ውስጥ እንዲዘፈቁ እና ከተቃራኒ እውነታዎች እንዲገለሉ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ፈተና እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ

በኢትዮጵያ ያለው የድኅረ-እውነት ፈተና ከምዕራባውያን ሀገራት በተለየ መልኩ እጅግ አደገኛ እና የሰዎች ሕይወት ላይ አደጋ የሚፈጥር እየሆነ ነው።

በጥቂት ጽንፈኞች የሚነዙ ስሜት ቀስቃሽ የፈጠራ ትርክቶች ሀገራችንን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሏት፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እንደ ጦር መሣሪያ ያገለገለው የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ምስክር ነው።

መንግሥት መረጃ የማጣራት ሥራ ቢሠራም፣ የቴክኖሎጂው ፍጥነት ለቁጥጥር ፈተና ሲሆን አስተውለናል።

በአሁኑ ወቅትም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረኩ እና ከሃይማኖት እንዲሁም ከብሔር ጋር የተያያዙ ሐሰተኛ የሤራ ትንተናዎች ማኅበራዊ ሚዲያውን አጥለቅልቀውታል።

ይህ የመረጃ መዛባት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተካሄደ ካለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት አንጻር ሲታይ አሳሳቢ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ሊሆን እና የዘመናት ቁስሎቻችንን ሊያክም የሚችለው፣ በሐሰተኛ ትርክቶች ያልተመረዘ፣ ለእውነት እና ለምክንያታዊነት የቆመ የሕዝብ ተሳትፎ ሲኖር ነው።

ነገር ግን የድኅረ-እውነት ፖለቲካ አራማጆች የሕዝቡን ስሜት በመኮርኮር፣ መተማመንን ለማሳጣት እና ልዩነቶችን ለማስፋት የሐሰት መረጃን በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።

በመሆኑም እውነተኛ ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የምክክር ሂደቱ ከሐሰተኛ የመረጃ ዘመቻዎች ሊጠበቅ ይገባል።

አሁን እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሩን ከዚህ ፈተና የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት። ማንኛውንም መረጃ ከማመናችን እና ከማጋራታችን በፊት "መረጃው ከየት መጣ? ምንጩስ ታማኝ ነው ወይ?" ብለን መጠየቅ ዘመኑ የሚጠይቀው ዋነኛ የዜግነት ግዴታችን ነው።

ስሜትን ከሚኮረኩሩ እና ሀገርን ወደ ግጭት ከሚመሩ የሐሰት ትርክቶች ራሳችንን በማራቅ፣ ሀገራችንን ከድኅረ-እውነት አደጋ በጋራ እንታደግ!

በለሚ ታደሰ
#ethiopia #posttruth #disinformation #factcheck #socialmedia #ebc

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.