Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ሕይወት) እያንዳንዱ ማለዳ ለአማኑኤል የጭንቀት ጊዜ ነው፤ ቀኑ የመጨረሻው የህይወት ዘመኑ ይሁን አይሁን አያውቅም። በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ ብዙ ጊዜ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ያለመጨረሻ ስንብት ወይም የመጨረሻ ምግብ የሚፈጸም ነው።

"እኔ በህይወት ያለሁ ሬሳ ነኝ" ይላል አማኑኤል። "ጓደኞቼ ከተገደሉ በኋላ እህል በአፌ አይዞርም፣ ውሃም አልጠጣም።"

አማኑኤል (ለደህንነቱ ሲባል የተቀየረ ስም) በሳዑዲ አረቢያ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ሀሚስ-ሙሻይት እስር ቤት ለበርካታ ዓመታት ከታሰሩ ወጣቶች አንዱ ነው። ሲኤንኤን ከእስር ቤቱ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት በዚህ እስር ቤት ውስጥ ብቻ ወደ 60 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ከአደገኛ ዕፅ ጋር በተያያዘ ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ይገኛሉ። ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ እስር ቤቶች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እየጠበቁ ነው። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እነዚህ ጉዳዮች የተናጠል እንዳልሆኑና የሳዑዲ ባለስልጣናት ሆን ብለው ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞችን ኢላማ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ። አብዛኛውን ጊዜ የእነዚህ ስደተኞች ዋነኛ "ወንጀል" የተሻለ ህይወት ፍለጋ ድንበር ማቋረጣቸው ብቻ ሆኖ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት በሳዑዲ አረቢያ በአጠቃላይ 356 ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት የተፈጸመ ሲሆን፣ ይህም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የታየው ከፍተኛው ቁጥር ነው። ከነዚህም ውስጥ 240ዎቹ በአደገኛ ዕፅ ወንጀል የተፈረደባቸው አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች ናቸው። ዘንድሮ ደግሞ አመጽ በሌለበት የአደገኛ ዕፅ ወንጀል የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሰዎች ቁጥር 71 የደረሰ ሲሆን፣ ከውጭ ዜጎች መካከል ኢትዮጵያውያን ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

በአውሮፓ የሳዑዲ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት የህግ ዳይሬክተር የሆኑት ጠበቃ ታሃ አል-ሀጂ፣ በሳዑዲ አረቢያ ስላለው የፍትህ ሂደት ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ተከሳሾች የህግ ድጋፍ እና በቂ የትርጉም አገልግሎት ስለማያገኙ፣ ምንም በማያውቁት ቋንቋ እና በድብደባ በተገኘ የእምነት ቃል የሞት ፍርድ እንደሚበየንባቸው ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። ይህ ፍትህ ሳይሆን ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚፈጸም የመንግስት ጥቃት መሆኑንም ተችተዋል።

የአማኑኤል ታሪክ በየዓመቱ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በየመን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚጓዙ የብዙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሰቆቃ የሚወክል ነው። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ከትግራይ ክልል የተሰደደው አማኑኤል፣ ሁለት ዓመታትን በየመን ካሳለፈ በኋላ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገባ። ለሶስት ወራት እረኛ ሆኖ ከሰራ በኋላ፣ አሰሪው እቃዎችን እንዲያጓጉዝ ስራ ሰጠው። አማኑኤል ስራ የሰጡትን ሰዎች አምኖ እቃውን ሲያጓጉዝ፣ በመኪናው ውስጥ ሀሺሽ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ዋለ።

"እኛ ተራ እቃዎች የምናጓጉዝ ብቻ ነው የመሰለን" የሚለው አማኑኤል፣ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በኤሌክትሪክ ገመድ እና በከባድ ድብደባ ሰቆቃ እንደተፈጸመበት ይናገራል። የፍርድ ቤቱ ሰነዶች በማያውቀው ቋንቋ የተዘጋጁ ሲሆን፣ ጠበቃም ሆነ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የመጣ ተወካይ አልነበረም። የሞት ፍርዱ በተላለፈበት አጭር የመጨረሻ ችሎት ላይ ብቻ አስተርጓሚ የቀረበ ሲሆን፣ ዳኛው ውሳኔውን አሳልፎ ይግባኝ የማለት መብት እንደሌለው ተነግሮታል።

"ጀርባዬ ላይ እጆቼን ጠምዝዘው በማሰር ደበደቡኝ፣ ለሶስት ሰዓታትም በፀሀይ ላይ ጣሉኝ። አሁን እምነቴን እንኳን በነጻነት ማራመድ አልችልም" ሲል አማኑኤል የደረሰበትን ግፍ ያስታውሳል።

የአማኑኤል እና መሰል ስደተኞች ቤተሰቦች ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ። የሞት ፍርድ ከተፈረደበት ሌላ እስረኛ ወንድም የሆነው ሰላም፣ "ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሳዑዲ መንግስት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ውሳኔው እንዲከለስ ሊያደርግ ይገባል፤ እባካችሁ ወንድሜን እና መሰሎቹን ታደጉልን" ሲል ተማጽኗል። እነዚህ ቤተሰቦች የፍርድ ውሳኔውን የሰሙት ከወራት በኋላ በዘመድ እና በማህበረሰቡ ወሬ እንጂ ከሳዑዲም ሆነ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት አይደለም።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ውይይት እንዲደረግ አጥብቀው እየጠየቁ ይገኛሉ። የሰዎች ህይወት በአጋጣሚ ወይም በፖለቲካ ፍላጎት ላይ ሊመሰረት እንደማይገባ የሚያስጠነቅቁት ባለሙያዎች፣ ስደተኞች የትርጉም አገልግሎት፣ የጠበቃ ጥበቃ እና ግልጽ የፍርድ ሂደት እንዲያገኙ በአፋጣኝ ፖሊሲዎች ሊከለሱ ይገባል ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የበርካታ ስደተኞች እና የቤተሰቦቻቸው እጣ ፈንታ አሁንም በከፍተኛ እርግጠኛ አለመሆን ውስጥ ወድቋል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.