Logo
EBC
የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት የሚያሻሽሉ ተግባራት ተከናውነዋል - አቶ ሙስጠፋ ሙሀመድ
****************

የሶማሊ ክልል የሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደሮች የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በስኬት ተጠናቅቋል።

በዚሁ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሀመድ፤ በበጀት ዓመቱ በሥራ አፈጻጸም የታዩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ማስቀጠልና የተመዘገቡ ድክመቶችንም ደረጃ በደረጃ እያረሙ ለበለጠ ስኬትና ልማት መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት የሚያሻሽሉ፣ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ ሀገራዊ ለውጡን ማግስት ጀምሮ በክልሉ በመንገድ መሠረተ-ልማት፣ በውኃ አቅርቦት፣ በጤና አገልግሎት እና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ዘርፎች የተመዘገቡ ታሪካዊ ዕድገቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልቅ እምርታ እያሳየ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ሙስጠፋ፤ በቀጣይም ማንኛውም ልማታዊ ፕሮጀክት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ ተጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቃ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው፤ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች የሕዝባዊ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቅለልና ለማዘመን በርካታ መዋቅራዊ የአሠራር ማሻሻዮችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት በክልሉ በስፋት የተጀመረውን የ"ፋይዳ" (ብሔራዊ) መታወቂያ አገልግሎት እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስኬታማ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተገበረ በሚገኘው የ"ኢትዮ ኮደርስ" የስልጠና ፕሮግራም አማካኝነት የበርካታ የክልሉ ወጣቶችና ዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ መቻሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው፤ ይህንን ዘመናዊ ዲጂታል ንቅናቄ በቀጣይም ይበልጥ ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ብሔራዊ ንቅናቄ አማካኝነት በሶማሊ ክልል የሚገኘውን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ይበልጥ ማነቃቃትና ማገዝ መቻሉን አብራርተዋል።

በቴዎድሮስ ታደሰ

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.