Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በታይላንድ ባንኮክ በተካሄደው ታላቅ የውበትና የሞዴሊንግ ውድድር ላይ ሀገሯን ኢትዮጵያን ወክላ የተሳተፈችው ሞዴል ሩት ሸዋታጠቅ የ"Miss Classy Model Earth 2026" አሸናፊ በመሆን አኩሪ ስኬት አስመዝግባለች።

ይህ ስኬት ለሩት የመጀመሪያዋ አይደለም። ከዚህ ቀደም የ"Miss Popularity" አሸናፊ መሆን የቻለች ሲሆን፣ በ"Miss International Ethiopia" እና በ"Miss ውበት Ethiopia" የውበት ውድድሮች ላይም ተሳትፋ የክብር ዘውድ ለመድፋት በቅታለች።

ሩት ሸዋታጠቅ ለስኬቶቿ ሁሉ መሠረት የሆኑትን ሁለገብ ስብዕናዎቿን ስታብራራ፣ በፈጣሪ ላይ ያላት ጠንካራ እምነት፣ በታዋቂው የናዝሬት ትምህርት ቤት ያሳለፈችው የትምህርት ቆይታ፣ በልጅነቷ በጀርመን ሀገር መኖሯ፣ እንዲሁም ሁለቱም ዶክተር ከሆኑት እናት እና አባቷ ያገኘችው አስተዳደግና ድጋፍ ለዛሬ ማንነቷ መገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ለዘ-ሐበሻ ገልጻለች።

ከተሳካው የሞዴሊንግ ህይወቷ ባሻገር በትምህርቷ እጅግ አስደናቂ ውጤት ያላት ሩት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርቷን በማዕረግ ያጠናቀቀች ሲሆን፣ በሀገር አቀፉ የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ላይም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የህግ ዲግሪ ባለቤት መሆን ችላለች። አሁን ላይም የህክምና ባለሙያ የሆነውን የአባቷን ፈለግ በመከተል በህክምና ትምህርት ዘርፍ የ"C2" ተማሪ ሆና ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች። በቆይታዋም የህክምና ተማሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን በምርጫ ተሰይማ በተሳካ ሁኔታ አገልግላለች።

ከእነዚህ ሙያዎቿ በተጨማሪ በስነ-ጥበብ ዘርፍ የዘፈንና የቅኔ (ግጥም) ተሰጥኦ ያላት ሲሆን፣ በተለይም በማህበራዊ ኃላፊነት ላይ በንቃት እየተሳተፈች ትገኛለች። ሩት "Ruth Drops" የተሰኘ የበጎ አድራጎት ተቋም በመመስረት በርካታ የህክምና እና ማህበራዊ ድጋፎችን ለህብረተሰቡ እያበረከተች ሲሆን፣ ከተግባራቶቿም መካከል በተስፋ አዲስ የካንሰር ማዕከል፣ በብሔራዊ የደም ባንክ እና በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚገኙ ህሙማንን በቁርጠኝነት መርዳቷ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።

እንኳን ደስ ያለሽ፣ ሩት!

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.