Logo
SeledaPost
ለእናቱ የገባውን ቃል ለመጠበቅ አስክሬን ቤት አስቀምጦ ለተፈተነው ታዳጊ ካሊድ ቃሲም የመኖሪያ ቤት ሊገነባለት ነው::

ከሦስት ሳምንታት በፊት እናቱ ባረፉበት ዕለት የገባውን ቃል ለማክበር ሲል አስክሬን ቤት ውስጥ ትቶ የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናውን በመፈተን መላውን የሀገሪቱን ሕዝብ በከፍተኛ ሐዘን ያስለቀሰውና ያስደመመው ታዳጊ ካሊድ ቃሲም፣ አዲስ የመኖሪያ ቤት ሊገነባለት መሆኑ ተሰማ።

በሸገር ከተማ አስተዳደር ኤካ ጣፎ ክፍለ ከተማ ከሁለት ታናናሽ ወንድሞቹ ጋር የሚኖረው ይህ የ14 ዓመት ታዳጊ፣ በወቅቱ እናቱ በጽኑ ታመው በነበሩበት ወቅት “እኔ አንድ ነገር ብሆን እንኳ ለዓመታት የለፋህበትን ፈተና እንዳታቋርጥ” በማለት ያስገቡትን ጥብቅ ቃል ለመጠበቅ የጠዋት ፈተናውን ተፈትኖ፣ ከሰዓት ደግሞ እናቱን አልቅሶና ቀብሮ በመመለስ የከሰዓት ፈተናውን ማጠናቀቁና “ቃልሽን አላጠፍኩም እማ!” ማለቱ ይታወሳል።

ዛሬ በተሰማው አዲስና ተስፋ ሰጪ መረጃ መሠረት፣ ለታዳጊውና ለታናናሽ ወንድሞቹ ቋሚ የቤት መፍትሔ ለመስጠት የሸገር ከተማ የኤካ ጣፎ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለቤት ግንባታ የሚሆን መሬት በይፋ አዘጋጅቶ አስረክቧል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የመኖሪያ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ገንብቶ ለታዳጊዎቹ ለማስረከብ ቃል ገብቷል።

ወላጅ አባቱ ከእነርሱ ርቆ በጅጅጋ ከተማ ሌላ ትዳር መሥርቶ በመኖሩ ምክንያት እናታቸውን አጥተው ብቻቸውን ለቀሩት ለእነዚህ ወንድማማቾች የተደረገው ይህ የመሬትና የቤት ግንባታ ድጋፍ፣ የታዳጊውን ታማኝነትና ብርታት ያከበረ እንዲሁም ማኅበራዊ አጋርነትን በተግባር ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።

Seledadotio
Seledadotio
3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.