Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በሀገር ቤት 321 ህፃናትን በልብ ቀዶ ጥገና ሞት አፋፍ ላይ ከመድረስ የታደገው 'ልብ ለልብ የህፃናት እርዳታ ፋውንዴሽን' (Heart to Heart Children's Aid Foundation)፣ አሁን ደግሞ ተጨማሪ 1,000 ህፃናትን ለማከም የጀመረውን ታሪካዊ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ዛሬ ምሽት ደማቅ የገቢ ማሰባሰቢያ እና የእራት ግብዣ አዘጋጅቷል።

ይህ ታላቅ የነፍስ አድን ስራ አካል መሆን ለሚሹ መላው የሚኒሶታ እና አካባቢው ነዋሪዎች፣ የዛሬው ልዩ ዝግጅት ምሽት 5:00 PM ላይ በብሉሚንግተን ከተማ፣ 475 E 78th St በሚገኘው አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ይካሄዳል።

በኢትዮጵያ ተመስርቶ በአሜሪካ ሀገር ህጋዊ እውቅናን በማግኘት የህፃናትን ህይወት በማትረፍ ላይ የሚገኘው ይህ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ በአሜሪካ ለሚያከናውነው የምስረታ ማስተዋወቂያና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ታዋቂውን ቲክቶከር አዶናይ ብርሃነን የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙ ይታወሳል። በዛሬው ዕለት በሚካሄደው በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ምሽት ላይም አምባሳደሩ በአካል በመገኘት የነፍስ አድን ዘመቻውን የሚያደምቅ ይሆናል።

ፋውንዴሽኑ መላው ማህበረሰብ የዚህ የተከበረ ቤተሰብ አባል በመሆን የህፃናቱን የነገ ተስፋ እንዲያለመልም ጥሪውን አስተላልፏል። የልብ ህመምተኛ የሆኑ ታዳጊዎችን ስቃይ ለማስታገስ እና በዚህ ታሪካዊ የነፍስ አድን ጉዞ ላይ የማይፋቅ አሻራን ለማሳረፍ ዛሬ ምሽት በዝግጅቱ ላይ መገኘትዎ ለአንድ ህፃን ዳግም ህይወት ማግኘት እጅግ የላቀ ትርጉም አለው።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.