Logo
YenetaTube
መንግሥት ያለ ምንም መዘግየት ወደ እውነተኛ ውይይት ይምጣ - ህወሓት

ህወሓት የአውሮፓ ህብረት ያወጣውን መግለጫ መቃወሙንና የሰላም ስምምነቱ አደጋ ላይ መውደቁን አስታወቀ

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የአውሮፓ ህብረት ልዑካን ቡድን በቅርቡ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ መሬት ላይ ያለውን እውነታ አያንጸባርቅም ሲል በጽኑ ተቃወመ።

የአውሮፓ ህብረት መግለጫ የተሳሳቱ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል በመግለጫው መሠረት ህወሓት ትይዩ ክልላዊ ምክር ቤት አቋቁሟል ተብሎ የቀረበበትን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል።

ድርጅቱ በክልሉ በምርጫ የተመረጠው ብቸኛው የትግራይ ክልላዊ ምክር ቤት በቅርቡ ሥራ መጀመሩን ገልጾ ይህ ምክር ቤት ወደ ሥራ ከመመለሱ በፊት በከተሞችና በገጠር ማህበረሰቦች ዘንድ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት በነዋሪዎች በወረዳና በጣቢያ ምክር ቤቶች ሙሉ ድጋፍ ያገኘ መሆኑን አስታውቋል።

ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በፌዴራል መንግስቱ ላይ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝሯል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የህዝቡን ጥቅም ማስጠበቅ ተስኖታል ያለው ድርጅቱ ይልቁንም እንደ ፌዴራል መንግስት አስፈጻሚ እየሰራ ነው ሲል ወቅሷል።

በተጨማሪም የሰላም ስምምነቱ (CoHA) ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ የፌዴራል መንግስት ስምምነቱን ለማዳከም እየሰራ መሆኑንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የስምምነቱን መሠረታዊ ሃሳቦች በተደጋጋሚ መካዳቸውን ገልጿል።

በዚህም ምክንያት የስምምነቱ ዋና ዋና ድንጋጌዎች ሳይፈጸሙ መቅረታቸውን በመግለጫው አመልክቷል።

ሰብአዊ ቀውስ እና የጸጥታ ስጋት
በትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት መቀጠሉን የጠቀሰው መግለጫው በተለይም
* በነዳጅ እና በንግድ ዕቃዎች ላይ የተጣለው ገደብ ከፍተኛ የዋጋ ንረትንና የኢኮኖሚ መገታት ማስከተሉን፣
* ተፈናቃዮች ያለ በቂ ድጋፍ የክረምቱን ዝናብ እየተጋፈጡ መሆናቸውን፣
* በክልሉ ዙሪያ እየተደረገ ያለው መጠነ-ሰፊ የወታደር ክምችት፣ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃቶችና የአየር ላይ ክትትሎች የጦርነት ስጋትን በከፍተኛ ደረጃ ማናራቸውን ዘርዝሯል።

ይህ ሁሉ እየሆነ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ በዝምታ መመረጡንና ፌዴራል መንግስቱ ግዴታውን እንዲወጣ ግፊት አላደረገም ሲል ኮንኗል።

ወታደራዊ የግዳጅ ምልመላ እና የወደፊት አቅጣጫ ላይ በሰፈረው የመግለጫው ማጠቃለያ ህወሓት አንድ ወገን ወታደራዊ ምልመላ እያካሄደ ነው ተብሎ የቀረበበትን ወቀሳ መሠረት ቢስ ነው ብሎታል።

ሆኖም የህልውና ስጋት ሲጋረጥ የትግራይ ባለስልጣናት ህዝቡን የመጠበቅና የመከላከል መብትና ኃላፊነት እንዳላቸው አስምሮበታል።

በመጨረሻም ድርጅቱ አሁንም ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ መሆኑንና የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ፖለቲካዊ ውይይት መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።

የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች የፌዴራል መንግስት ያለ ምንም መዘግየት ወደ እውነተኛ ውይይት እንዲመጣ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቧል።

3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.