Logo
FBC
በብራዚል ብሔራዊ ቡድን እየደመቀ የሚገኘው ቪኒሸስ ጁኒየር…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሸስ ጁኒየር በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ዋንጫ ውድድር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ብራዚላዊው የፊት መስመር ተጫዋች ቪኒሸስ ጁኒየር ሀገሩ ጥሎ ማለፉን እንድትቀላቀል ትልቁን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ብራዚል በ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሞሮኮ ጋር አንድ አቻ በሆነ ውጤት ስትለያይ የአቻነቷን ግብ ያስቆጠረው ቪኒሸስ ጁኒየር ነበር፡፡

በሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ብራዚል ሄይቲን 3 ለ 0 ስታሸንፍ በጨዋታው ቪኒሸስ ጁኒየር አንድ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡በምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ብራዚል ስኮትላንድን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ቪኒሸስ ጁኒየር በ2026 የዓለም ዋንጫ በሦስት የምድብ ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች መካከል ይገኛል፡፡

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ከሊዮኔል ሜሲ በአንድ ግብ በማነስ ከኪሊያን ምባፔ እና ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ እኩል አራት ግቦችን በማስቆጠር ለወርቅ ጫማው እየተፋለመ ነው፡፡

ቪኒሸስ ጁኒየር በዓለም ዋንጫ የምድብ እያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረ አምስተኛው ብራዚላዊ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ከዚህ ቀደም የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆኑት ጃይርዚንሆ (1970)፣ ሮማሪዮ (1994)፣ ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ እና ሪቫልዶ (በ2002) በእያንዳንዱ የምድብ ጨዋታ ግብ ማስቆጠራቸው ይታወሳል፡፡

ተጫዋቹ በሦስቱም የምድብ ጨዋታዎች ግብ ከማስቆጠር ባለፈ በእያንዳንዱ ጨዋታ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።ቪኒ ሀገሩ ብራዚል ምድቧን በበላይነት እየመራች ወደ ጥሎ ማለፉ እንድትገባ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከቀድሞ አሰልጣኙ ካርሎ አንቸሎቲ ጋር በብራዚል ብሔራዊ ቡድን የመገናኘት ዕድል ያገኘው ቪኒሸስ ጁኒየር በዓለም ዋንጫው ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ በስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ቪኒሸስ ጁኒየርን ማሰልጠናቸው ይታወሳል፡፡በአሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ሥር በሪያል ማድሪድ ቤት ምርጥ እንቅስቃሴ ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል ቪኒሸስ ጁኒየር አንዱ ነው፡፡

ተጫዋቹ ከምድብ 3ኛ ዙር ጨዋታ በኋላ በሰጠው አስተያየት÷ ከአሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ጋር መስራት እንደሚወድ እና አንቸሎቲ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አሰልጣኞች መካከል ናቸው ሲል ተደምጧል።

ጊዜው ሲደርስ በብራዚል ብሔራዊ ቡድን እንደገና ምርጥ ብቃቴን እንደማሳይ እርግጠኛ ነበርኩ ብሏል።
በ2026 የዓለም ዋንጫ በምድብ 3ኛ ጨዋታ ለሀገሩ ብራዚል የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ኔይማር ጁኒየር በዚህ የዓለም ዋንጫ ቪኒሸስ ጁኒየር የእኛ ኮከብ በማለት አሞካሽቶታል፡፡

በዓለም ዋንጫው ጥሩ ጅማሮ ላይ የሚገኘው ቪኒሸስ ጁኒየር በቀጣይ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ተጠባቂ ናቸው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.