Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) ) ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በፊት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ በተካሄደ ምርጫ ተቋቁሞ የነበረው እና በቅርቡ ዳግም ወደ ሥራ የተመለሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፣ በቅርቡ ያጸደቀው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ አዋጅ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ ማስተላለፉ ተጋለጠ። ይህ እርምጃ ክልሉ ከጦርነት ማግስት ወደ መልሶ ግንባታ እና ሰላም እያመራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ዳግም ወደ ወታደራዊ ማሰባሰብ እያመራ መሆኑን የሚያሳይ እና አሳሳቢ የህግ ጥሰት የታየበት ሆኗል።

የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ መሆናቸው የተነገረላቸው ወ/ሮ ምኅረት ሃጎስ፣ ሰኔ 17 ቀን ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ፣ አዋጁ በመደበኛነት በክልሉ ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ ድረስ የክልሉ የፍትሕ አካላት በጊዜያዊነት እየሠሩበት እንዲቆዩ ማዘዛቸውን ዋዜማ ያየችው ሰነድ ያረጋግጣል። ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ግልባጭ የተደረገው ይህ ትዕዛዝ፣ አንድ ህግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ለህዝብ ይፋ ሳይደረግ ተግባራዊ እንዲደረግ ማዘዙ መሰረታዊ የህግ አሰራርን እና የዜጎችን መብት የጣሰ ድርጊት መሆኑን ያሳያል።

ይህንን የግዳጅ ምልመላ አዋጅ በበላይነት ለማስፈጸምም ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት አዲስ "ማዕከላዊ የጸጥታ ዕዝ" መቋቋሙ የጉዳዩን አሳሳቢነት ይበልጥ አጉልቶታል። አዲስ የተቋቋመው ይህ ወታደራዊ መዋቅር ክልሉ ያለበትን የሽግግር ጊዜ ፖለቲካዊ እና ጸጥታ ነክ ስጋቶች ሊያባብስ እንደሚችል ተገምቷል።

የምክር ቤቱ የግዳጅ ምልመላ እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከባድ ተቃውሞ ገጥሞታል። ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች የትግራይ ባለሥልጣናት ይህንን አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሱ ሰሞኑን አጥብቆ መጠየቁ ይታወሳል። የጦርነቱን አሰቃቂ ጠባሳ ገና ያልሻረው የክልሉ ወጣት ወደ ትምህርት እና መደበኛ ህይወቱ መመለስ ሲገባው፣ ያለ ህጋዊ የህትመት ሂደት በግዳጅ ወደ ውትድርና እንዲገባ መደረጉ፣ የክልሉን አመራሮች የፖለቲካ ፍላጎት እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ አያያዝ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው።

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.