Logo
EBC
ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የመገናኛ ብዙኃን የንቅናቄ ዘመቻ አስጀመረ
*************

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን ለማሳካት የሚያስችል የንቅናቄ ዘመቻ ለመጀመር በኢትዮጵያ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር፣ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም እና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) መገናኛ ብዙሀን ከኮሚሽኑ ጋር በመስራት እስካሁን ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ቀጣዩ ሀገራዊ ጉባኤ ከቅድመ ጉባኤ ጀምሮ ጥንቃቄ የተሞላበት የአዘጋገብ ስልት ስለሚጠይቅ ይህንን ለማስገንዘብ እና ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ ለመጀመር መድረኩ መዘጋጀቱን አክለዋል።

መገናኛ ብዙሀን የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት ሲዘግቡ በአካታችነት መርሁ መሰረት የሁሉንም ዜጎች ድምፅ በማካተትት፣ የኮሚሽኑን ነፃና ገለልተኛ አሰራር በመጠበቅ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መግባባት ለመፍጠር በሚያግዝ መልኩ መሆኑን እንዳለበት ነው አፅንኦት ሰጥተው ያስገነዘቡት።

ከቅድመ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እስከ ድህረ ጉባኤ መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ እና ተደራሽ መረጃ በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡም አክለዋል።

በመድረኩ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዮሀንስ ሽፈራው (ዶ/ር) ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመጥቀስ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን መገናኛ ብዙሀን ሊከተሏቸው የሚገቡ የአዘጋገብ ስልቶችና ሙያዊ ስነምግባሮችን አመላክተዋል።

የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች በበኩላቸው የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለሕዝብ በስፋት ለማስተዋወቅና በሂደቱ ዙሪያ የሚቀርቡ መረጃዎች ተዓማኒነት እንዲኖራቸው በትኩረት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።

በዕለቱ ኮሚሽኑ በራሱ የውስጥ አቅም ያዘጋጃቸውን 15 የክልል የምክክር መድረክ ዘጋቢ ፊልሞች፣ 19 የቴሌቪዥንና የማህበራዊ ሚዲያ የቅስቀሳ መልዕክቶችን፣ 6 የሬዲዮ መልዕክቶችን እንዲሁም በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ አጫጫር መልዕክቶችን ለሚዲያ አመራሮቹ አስረክቧል።

ኮሚሽኑ ያስረከባቸው መልዕክቶች መገናኛ ብዙኃኑ በራሳቸው አቅም ከሚያዘጋጇቸው ተጨማሪ ሆነው እንደ ግብዓት እንደሚያገለግሉ ተነግሯል።

መልዕክቶቹን ከመጪው ሰኞ ሰኔ 15/2018 ዓ.ም ጀምሮ በስፋት ወደ ሕዝብ ለማድረስ በኮሚሽኑና በመገናኛ ብዙሀኑ መካከል መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዚህ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ከ80 በላይ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮና የሕትመት ሚዲያ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሞያዎች እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮሚ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የትራንስፓርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የኮሙኒኬሽን ሀላፊዎች እና የተለያዩ የክብር እንግዶች ተሳትፈዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 50 የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሀን ሀላፊዎችንና ባለሙያዎችን ያገኘበት መድረክ አከናውኖ ተመሳሳይ የሚዲያ ንቅናቄ ዘመቻ ማስጀመሩ ይታወሳል።
#ethiopianbroadcastingcorporation #ethiopiannationaldialoguecommission #nationaldialogue #mediacampaign #peaceandunity

4 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.