Logo
EBC
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በሰብአዊነት፣ ብሔራዊ አንድነት እና ሁለንተናዊ ሪፎርም ላይ አዲስ የአመራር ምዕራፍ እያስመዘገቡ ነው” - የዱባይ ዶት ኒውስ ጋዜጠኛ ጄራርድ ኡርባኖዞ
************************

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ዜና ኔትወርክ በሆነው የዱባይ ዶት ኒውስ ጋዜጠኛ ጄራርድ ኡርባኖዞ በጻፈው ሐተታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰብአዊነትን እና ሁለንተናዊ ሪፎርምን ማዕከል ያደረገ የአመራር ጉዞ እያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብአዊነትን፣ ማኅበራዊ አገልግሎትን እና ብሔራዊ አንድነትን ያቀናጀ አዲስ የአመራር ምዕራፍ በኢትዮጵያ እያሰፈኑ መሆናቸውንም አመልክቷል።

ከመጀመሪያው የአመራር ቀናቸው ጀምሮ መቻቻልን እና አንድነትን የፖለቲካ ማዕቀፍ ማድረጋቸውን የሚገልጸው ጽሑፉ፣ በወቅቱ የነበረውን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መከፋፈል ለመፍታት ለብሔራዊ አንድነት እና አብሮ መኖር ቅድሚያ መስጠታቸውን አስረድቷል።

ይህንን ሕዝባዊ ወገንተኝነታቸውን በተግባር ለማሳየትም ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ማዕድ ከመጋራት ጀምሮ የደካሞችን ቤት እስከማደስ እና ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የሀገር መሪዎችን በራሳቸው መኪና እየነዱ ማስተናገዳቸውን አብራርቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ መሪነት ከመምጣታቸው በፊት በተለያዩ ቦታዎች በኃላፊነት ማገልገላቸውን የሚገልጸው ጽሑፉ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ትላልቅ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ለውጦችን ማከናወናቸውን አስታውሷል።

በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መፈታታቸውን፣ ‘አሸባሪ’ ተብለው ከተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይቶች መደረጉን፣ የሕግ እና የፍትሕ ማሻሻያዎች መጀመሩን እንዲሁም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መከናወናቸውን አስረድቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የብዝኃነት ማኅበራዊ መሠረት ወደ የወል፣የተስማማ እና የበለጸገ ስብስብ ለመቀየር በማለም ሀገር በቀል የ‘መደመር’ ፍልስፍናን በዋናነት እንደተጠቀሙም አብራርቷል።

ጋዜጠኛ ጄራርድ ኡርባኖዞ በጽሑፉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩን በስፋት ያተተ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ማስጀመራቸውን አመልክቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ 65 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል በያዘችው ብሔራዊ ግብ መሠረት የዘንድሮውን ሳይጨምር 48 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አብራርቷል።

መርሐ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት የሳበ ንቅናቄ መሆኑንም ጠቅሷል።
#ethiopia #ebc #pmabiyahmed #dubaidotnews

3 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.