Logo
YenetaTube
IMF ለኢትዮጵያ የ468 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ የሚያስገኝ የስምምነት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታወቀ

የኔታ ሚዲያ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የባለሙያዎች ቡድን እና የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር ማዕቀፍ (ECF) አምስተኛው ክለሳ ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ድርጅቱ አስታወቀ።

ይህ በባለሙያዎች ደረጃ የተደረሰው ስምምነት በIMF ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሲጸድቅ ኢትዮጵያ ወደ 468 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት የምትችል ይሆናል።

በአልቫሮ ፒሪስ የተመራው የIMF የባለሙያዎች ቡድን ከአምስተኛው ክለሳ ጋር በተያያዘ ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በአካል ከዚያ በኋላ ደግሞ በበይነ መረብ (ቨርቿል) ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።

የልዑካን ቡድኑ መሪ አልቫሮ ፒሪስ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳቸውን በተሳካ ሁኔታ መተግበራቸውን መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

እ.ኤ.አ እስከ 2026 መጀመሪያ ድረስ የምርት አመላካቾች፣ ወጪ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እና የመንግሥት ገቢ መሻሻል ማሳየታቸውንና የዋጋ ንረትም መቀነሱን ጠቁመዋል።

ሆኖም በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰው ጦርነት በንግድ እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል መፍጠሩን፣ ጊዜያዊ የነዳጅ እጥረት ማስከተሉን እና የገቢ ነዳጅና ማዳበሪያ ዋጋን በከፍተኛ ሁኔታ ማናሩን መግለጫው አመልክቷል።

ይህ ትልቅ ውጫዊ ተጽዕኖ ቢሆንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አሁንም ጠንካራ መሆኑንና በምርት ዕድገትና በሸማቾች ዋጋ ንረት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እስካሁን መጠነኛ መሆኑ ተገልጿል።

የIMF መግለጫ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት ዓለም አቀፋዊ አለመረጋጋትና የሸቀጦች ዋጋ መዋዠቅ በመጨመሩ፣ በኢኮኖሚው ላይ ሊደቀኑ የሚችሉ ስጋቶች መጨመራቸውን ያስጠነቅቃል። በመሆኑም ለነዚህ አዳዲስ ተግዳሮቶች ብልህ ምላሽ መስጠትና የሀብት አጠቃቀምን በጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚከተሉት መሠረታዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ድርጅቱ መክሯል፦

• የገንዘብ ፖሊሲ ማጥበቅ፦ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን ማስቀጠል።
• የውጭ ምንዛሬ ገበያ ማሻሻያ፦ የውጭ ምንዛሬ ገበያው ይበልጥ ግልጽና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲሠራ ማድረግ።
• የአገር ውስጥ ገቢና ወጪ አስተዳደር፦ የአገር ውስጥ ገቢ ማሰባሰብን ማሳደግና የወጪ አስተዳደርን በጥንቃቄ በመምራት የፋይናንስ ዘላቂነትን ማረጋገጥ።

• መዋቅራዊ ማሻሻያዎች፦ የንግድ አካባቢን ማሻሻል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጥንካሬ ማጠናከርና የግል ዘርፉ መር ለሆነ ዕድገት በር መክፈት።

የውጭ ዕዳ ሽግሽግ

የኢትዮጵያን የዕዳ ዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ሽግሽግ (treatment) ለማግኘት መልካም ግስጋሴ እየታየ መሆኑን IMF ገልጿል። ከባለሥልጣናት አበዳሪዎች ጋር የሚደረገው የዕዳ መልሶ ማዋቀር ውይይት እንደተጠበቀው እየገፋ ሲሆን ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚደረገው ድርድርም መቀጠሉ ተጠቅሷል።

የIMF ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ በነበረው ቆይታ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ እና ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከግል ዘርፉና ከልማት አጋሮች ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን በመግለጽ ለተደረገለት ትብብር ምስጋና አቅርቧል።

ይህ አምስተኛው ክለሳ በIMF ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሲጸድቅ ኢትዮጵያ በዚሁ ማዕቀፍ እስካሁን ያገኘችው አጠቃላይ የገንዘብ ድጋፍ ወደ 2.65 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ይላል።

15 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.