Logo
EBC
ኢትዮጵያውያን መርጠዋል፤ ኢትዮጵያ አሸንፋለች! - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
***********************

ኢትዮጵያ ከዜጎቿ የፈለገችውን ኹሉ በፈለገችው ጊዜና ኹኔታ የምታገኝ ሀገር ናት። ለሀገራቸው የተጠየቁትን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ ዜጎች ስላሏት በእጅጉ ኮርታለች። ከዓድዋ እስከ ሕዳሴ ግድብ፣ ከወገን ለወገን መረዳዳት እስከ አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎቿን ተሳትፎ ጠይቃ፣ ከመሻቷ በላይ ተሳትክቶላታል። ዛሬ የተደገመውም ይኸው ነው።

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን ማንበር፣ በግልጽና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥትን መምረጥ፣ ሕገ መንግሥታዊነትን ፅኑ መሠረት ማስያዝ ትሻለች። ለዚህ ደግሞ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ እንደ ትልቅ አጋጣሚ መጠቀም አስፈልጓት ነበር።

በምላሹም ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመራጭነት ተመዝግበው የዛሬዋን ቀን ሲጠባበቁ ቆይተዋል። እነሆ የእናት ሀገር ጥሪን በመቀበል ዜጎች በነቂስ ወጥተው ሲመርጡ ውለዋል፤ ሌሊቱንም አጋምሰዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ዜጎች ለረዥም ሰዓታት ተሰልፈው ድምፅ የሰጡበት ልዩ ምርጫም ነው።

ምርጫው እንዳይካሄድ ባዳ እና ባንዳ ተቀናጅተው ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልደረደሩት እንቅፋት አልነበረም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለጠራችው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የማይቻል ነገር አልነበረምና በስኬት ተጠናቅቋል። ኢትዮጵያውን በሰላማዊ መንገድ መርጠው ኢትዮጵያ አሸንፋለች።

የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጥሪ ተቀብሎ ከንጋት እስከ ምሽት በመምረጥ ምላሽ ለሰጠው ሕዝብ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱ እንዲጸና እና ዜጎች በሰላም እንዲመርጡ ምቹ ዓውድ ለፈጠሩ የፀጥታ አካላት፣ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየደቂቃው ሲያደርሱ ለነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲሁም የምርጫውን ሂደት ለመሩ፣ ላስተባበሩ እና ለታዘቡ ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች።

የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ግንቦት 25 2018፣ አዲስአበባ፣ ኢትዮጵያ
#ebc #ethiopia #gcs

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.