Logo
EBC
የኢትዮጵያ አዲሱ የቃል-ኪዳን ድልድይ፡ ከቂም በቀል ስብራት ወደ ምክክር መድኃኒት!
*********************
( የዕለቱ መልዕክት)

ቂምን አዝሎ መሮጥ መድረሻው ገደል ነው እንዲሉ ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በታሪካዊና መዋቅራዊ ስብራቶች ውስጥ የቆየችው ያለፈውን ቁስል በዝምታ ሸፍኖ፣ ነገን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመቅረጽ በመሞከሯ ነው። ዛሬ ግን ይህንን የጥፋት አዙሪት የሚሰብር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል።

መንግሥት እንደ ትልቅ የሰላም ምሰሶ የተጠቀመበት ትናንትን በሽግግር ፍትሕ የማረም፣ ነገን ደግሞ በሀገራዊ ምክክር የመገንባት" ስትራቴጂ፣ ሀገራችን ለዘመናት ስትጠብቀው የነበረው የሰላም ድልድይ ነው።

ያለፉ በደሎች እና ግጭቶች ሳይታረሙና ተገቢው ፍትሕ ሳይሰጥ ወደ ፊት ለመጓዝ መሞከር የቆሰለን እግር ሳይታከሙ ለሩጫ እንደመዘጋጀት ይቆጠራል።

የሽግግር ፍትሕ ያለፈውን ሸክም የሚያቀልል ሲሆን ሀገራዊ ምክክር ደግሞ የነገውን መንገድ የሚጠርግ በመሆኑ ሁለቱ ሂደቶች የማይነጣጠሉና ተመጋጋሚ የሰላም መሣሪያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነቶችና ጥንታዊ እሴቶች ባለቤት ብትሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ የተቀነቀኑ የበደል ትርክቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታው ትልቅ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

ይህንን ስብራት ለመጠገን የተወጠነው ሀገራዊ ምክክር ግን ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ነው። ምክክሩ፡፡ “ለካስ ስለ ሀገሬ እኔም መምከር እችላለሁ፤ ለካስ የእኔም ድምፅ ይሰማል” የሚሉ ዜጎች ወደ ምክክሩ ቀርበዋል።

ከወረዳ እስከ ፌደራል፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቁጭ ብለው በጋራ እንዲመክሩ መደረጉ፣ ሂደቱ ምን ያህል አካታችና ተዓማኒ እንደሆነ ማሳያ ነው። የተበታተኑ ሐሳቦች ወደ አንድ የጋራ አጀንዳ መምጣታቸው ለሀገራዊ መግባባት የጸና መሠረት ይጥላል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት ትልቅ ፋይዳ አላቸው። በቅርቡ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ወገኖች ሰላምን መርጠው ወደ ምክክር መድረኩ መምጣታቸው፣ የሐሳብ የበላይነት ከጠመንጃ ኃይል እንደሚበልጥ በተግባር ያሳየ ስኬት ነው።

ዛሬ ላይ የምናደርገው ምክክር የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ይወስናል። የቂም ቁርሾን ለትናንት ትተን፣ በፍቅር እና በውይይት የምትመራ፣ ለልጆቻችን የምትመች እና በሁለንተናዊ ብልጽግና የደመቀች ኢትዮጵያን መገንባት የትውልዱ የቤት ሥራ ነው።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ታላቁ ጉባኤ ሲጀመር፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሂደቱን በባለቤትነት ሊደግፈውና ሊሳተፍበት ይገባል።

የሀገራችንን ሰላም በጋራ ጥረት የምናጸናበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን በሰለጠነ ባህል የምትፈታ ሀገር እንድትሆን፣ ይህ ታሪካዊ የምክክር ጅማሮ ወደ ስኬት እንዲሻገር ሁላችንም የሰላም ጀግኖች ልንሆን ይገባል። ነገ ለልጆቻችን የምናወርሰው ሀገር በዛሬው ምክክራችንና በምናሳየው መቻቻል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ይህንን ወርቃማ ዕድል መጠቀም የታሪክ አደራ ነው።

የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል

22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.