Logo
FBC
ከኒኮቲንና ትምባሆ ነጻ ቀን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በየዓመቱ ግንቦት ወር ላይ ትምባሆ መጠቀም ወይም ለትምባሆ ጭስ መጋለጥ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ሊያስገነዝቡ በሚችሉ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

በተለይም መንግሥታት፣ ህብረተሰቡና ውሳኔ ሰጪ አካላት የትምባሆን ዘርፈ ብዙ የጤና ጉዳቶችና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመገንዘብ ቁጥጥሩን እንዲያግዙ ጥሪ ይቀርብበታል።

ዘንድሮም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ39ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገራችን ለ34ኛ ጊዜ ‘ለኒኮቲንና ለትምባሆ ሱሰኝነት አጋላጭ የሆኑ ስልቶችን እናጋልጥ’ በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ በዋናነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የትምባሆ እና የኒኮቲን ምርቶች አጠቃቀም ድብቅና አሳሳች መረጃዎችንና የተለያዩ ስልቶችን በተመለከተ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡

በዚህም መሰረት የዚህ ዓመት የዓለም የትምባሆና ኒኮቲን ነጻ ቀን ዋና ዓላማ ከሱሰኝነት መከላከልና ወደፊት የሚኖረውን የአጫሾች ቁጥር መቀነስ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።

የትንባሆ አጠቃቀም ለበርካታ የጤና ስጋቶች አጋላጭ መሆኑን የሚገልጸው ባለሰልጣኑ፤ አፋጣኝ እና የረጅም ጊዜ ጉዳት፡ ልብ እና ደም ዝውውር፣ የመተንፈሻ አካላት እና ስኳር በሽታን ጨምሮ ከ20 በላይ ለሚሆኑ የካንሰር አይነቶች እንደሚያጋልጥ ያብራራል።

በየዓመቱ በዓልም ላይ ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከትምባሆ ጋር በተያያዘ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሲሆን፤ ህጻናትን ጨምሮ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን አጫሽ ያልሆኑ ሰዎች ሌሎች በሚያጨሱት የተነሳ ለሞትና ለበሽታ ይዳረጋሉ።

ችግሩን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የትንባሆ ኢንዱስትሪው አሳሳች ስልቶችን በመጠቀም አዳጊዎችን ዋነኛ ኢላማ አድርገው መንቀሳቀሳቸው ከፍተኛ ፈተና መሆኑ ይነገራል።

ምርቶቹ ማራኪ እንዲሆኑ እንደ ቸኮሌት፣ ቫኒላ እና ፍራፍሬ ያሉ ጣዕሞችን መጠቀማቸው እንዲሁም ሲጋራን በረቀቀ ቴክኖሎጂ (እንደ ኢ-ሲጋራ) መተካት ችግሩን ያወሳስበዋል።

በመሆኑም የኢንዱስትሪውን ተለዋዋጭ ስልቶች በማጋለጥ ችግሩን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል።

በመሆኑም መንግሥት፣ ሚዲያ፣ ወላጆች እና ሲቪክ ማህበራት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል።

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.