Logo
FBC
ከጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ እስከ ቆሜ ልመርቅሽ...

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በነበረው ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሙዚቃው ንጉሥ በሚል መጠሪያ ይታወቃል ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ።

ስመ ገናናው፤ ድምጹ በሁሉም ቤት የተሰማውና በሁሉም ትውልድ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ጠመንጃ ያዥ ሰፈር ተወልዶ በወሊሶ ከተማ አደገ።

በ1950ዎቹ መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት መጀመሪያ ሀገር ፍቅር ቴአትርን በኋላም የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድንን ተቀላቅሎ በድምጻዊነት በቁጥር ይህን ያህል ናቸው የማይባሉ እጅግ በርካታ ዘፈኖችን ተጫውቷል።

ከልጅነት ጀምሮ ለሙዚቃ የነበረው ፍቅርና ልዩ ተሰጥኦ በወቅቱ በነበሩ የጥበብ ሰዎች ዘንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲታወቅ አድርጓል።

ጥላሁን በጥበብ ሕይወቱ ስለ ኢትዮጵያ ሲቀኝና ሲዘምር የኖረ ልዩ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅርንም ያስተማረ ታላቅ የጥበብ ሰው ነበር።

የፍቅርን ጥልቀት፣ የናፍቆትን ጽኑነት፣ የሀገርን ፍቅርና የማሕበራዊ ህይወትን ውጣ ውረድ በዜማዎቹ ዳስሷል።

የአርቲስቱ ሥራዎች ዛሬም ድረስ እንደ አዲስ የሚደመጡ እና የማያረጁ የጥበብ ውጤቶች ሆነው ቀጥለዋል።

በሀገር ፍቅር "ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ"ን በመጫወት በይፋ የተጀመረው የጥላሁን የግማሽ ምዕተ ዓመት የሙዚቃ ሕይወት "ቆሜ ልመርቅሽ" በሚሰኘውና ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ባስቀረፀው የመጨረሻው አልበም ነው የተደመደመው።

አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ለሀገሩ የሙዚቃ ዕድገት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ሲሆን÷ በተጨማሪም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በርካታ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝቷል።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ይህን ታላቅ ከያኒ ለመዘከር እና ለህያው ሥራዎቹ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በአፍሪካ ፓርክ የመታሰቢያ ሐውልት አቁማለታለች።

በሶስና አለማየሁ

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.