Logo
FIDEL POST NEWS
ለ6 ሺህ ህፃናት ተስፋ የሆነው የሆፕ ኤስ.ቢ.ኤች የ2026 ብሔራዊ ዘመቻ ተጠናቀቀ

​በህብለ-ሰረሰር ዘንግ ክፍተት እና በጭንቅላት ውስጥ ፈሳሽ መከማቸት ችግር ያለባቸው ህፃናት ትምህርት የማግኘት መብታቸው እንዲከበር የሆፕ ኤስ.ቢ.ኤች ጥሪ አቀርቧል።

ድርጅቱ ይህንን ጥሪ ያስተላለፈው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የቆየውን የ2026 ብሔራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ በስኬት ማጠናቀቁን ተከትሎ ነው።

የድርጅቱ መስራች ወ/ሮ ቤዛ በሻህ "የእውቀት ማህደር ውስጣቸው ተቀብሯልና ልጆቻችን ትምህርት ያግኙ!" በማለት ማህበረሰቡና መንግስት ለህፃናቱ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

​ዘመቻው በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከ200 በላይ ተማሪዎች፣ የፓርላማ አባላትና አርቲስቶች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጅቷል ተብሏል።

ድርጅቱ በማዕከሉ በኩል ለተረጂ ቤተሰቦች የፊዚዮቴራፒ፣ የአእምሮ ጤና እና የንግግር ህክምና ድጋፎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

እነዚህ ተግባራት ችግሩ ባለባቸው ህፃናትና በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ተስፋን የፈጠሩና ማህበረሰባዊ ግንዛቤን ያሳደጉ እንደነበሩ ተገልጿል።

​በክልሎች ደረጃም አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በድሬዳዋ አስተዳደር አራት የነርቭ ቀዶ ጥገናዎች እንዲከናወኑ ከመመቻቸቱ ባለፈ ከ5,000 በላይ የትምህርት ቁሳቁሶች በሦስት ቋንቋዎች ተሰራጭተዋል።

በአፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ እና አማራ ክልሎችም የፖሊሲ ውይይቶች፣ የቀዶ ጥገና ድጋፎች እና የነርቭ ዘንግ ክፍተት መከላከያ አውደ ጥናቶች በድምቀት ተካሂደዋል።

ይህም ዘመቻው የከተማ ማዕከላትን ብቻ ሳይሆን ገጠራማ የሀገሪቱ ክፍሎችንም ተደራሽ ማድረጉን ማሳያ ነው ተብሏል።

​በአሁኑ ወቅት ከ6,000 በላይ ህፃናትን በቋሚነት እየረዳ የሚገኘው HOPE-SBH፣ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል።

ድርጅቱ በቀጣይም የህፃናቱን ሁለገብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
3 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.