Logo
FIDEL POST NEWS
​"ከኻሜኒ አጠገብ የተቀመጠው ከዳተኛ"፦ እስራኤል የኻሜኒን መገኛ እንዴት አወቀች?

​​ለ37 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩትን የመካከለኛው ምስራቅ አንጋፋ መንፈሳዊ መሪ ኢላማ ያደረገው ይህ ኦፕሬሽን፣ በአጋጣሚ ወይም በጭፍን ወታደራዊ ኃይል የተፈጸመ እንዳልሆነ ተነግሯል። ቅዳሜ ጠዋት በኻሜኒ የሚመራው ከፍተኛ ስብሰባ እየተካሄደ በነበረበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሰላሳ በላይ ከባድ ቦምቦች አርፈዋል።

​የክስተቱ አስገራሚው ገጽታ ቦምቡ ሳይሆን፣ ኢላማው የተመረጠበት የቀዶ ጥገና ያህል ጥንቃቄ የተሞላበት ትክክለኛነት ነው። የሞሳድ ሰራተኞች ስለ ስብሰባው ሙሉ ምስል እንደነበራቸው ተዘግቧል፦ የስብሰባውን ትክክለኛ መጀመሪያ ሰዓት፣ የውይይቱን ርዕሰ ጉዳይ፣ ተሳታፊዎችን እና ሌላው ቀርቶ የክፍሉን አቀማመጥ ጭምር ያውቁ ነበር።

​እንደ ኢራን ግምት ከሆነ፣ የእስራኤል የስለላ ድርጅት በጥቃቱ ወቅት ኻሜኒ የነበሩበትን ቦታ በዝርዝር ያውቅ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ መረጃ በሳተላይት ወይም በኤሌክትሮኒክስ ጠለፋ ሊገኝ አይችልም፤ ሊገኝ የሚችለው በአካባቢው በአካል ከነበረ የሰው ምንጭ ብቻ ነው።

ፍንጮቹ እውነት ከሆኑ፣ ለመንፈሳዊው መሪው የቅርብ ክበብ ውስጥ ያለ ሰው ወሳኝ መረጃን ለእስራኤል አሳልፎ ሰጥቷል ማለት ነው። ይህም ጥቃቱ እንደተለመደው በምሽት ሳይሆን በቀን የተፈጸመበትን ምክንያት ያብራራል።

የዜና ​ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፣ ከጥቃቱ በኋላ የመንፈሳዊው መሪውን ሞት የሚያረጋግጥ ምስል ወዲያውኑ ተላልፏል። ወደ ስፍራው የተጠጋው ወኪል በሞባይል ስልኩ ቪዲዮ በመቅረጽ፣ የሟቹን ማንነት ለማረጋገጥ በሟቹ እጅ ላይ የነበረውን ልዩ ቀለበት አሳይቶ ፎቶዎቹን በቀጥታ ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ልኳል።

በዚህም የአያቶላው ረዳቶች ምን እንደተፈጠረ እንኳ ከመገንዘባቸው በፊት የእስራኤሉ መሪ ስለ ኻሜኒ ሞት ቀድመው መረጃ ደርሷቸዋል።

​በመቀጠል ኔታንያሁ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መረጃውን አጋርተዋል። የአሜሪካው መሪ በ"ትሩዝ ሶሻል" ማህበራዊ ገጽ ላይ የሰጡት መግለጫ የሟቹን ማንነት የሚያረጋግጡ መረጃዎች ከተለዋወጡ በኋላ እንደመጣ ተነግሯል።

ይህ ቅደም ተከተል ኢራን ይፋዊ አቋሟን ከማሳወቋ በፊት እስራኤል የተረጋገጠ መረጃ እንደነበራት ያሳያል።

​ጄኔራል ቃአኒ በጥሪጣሬ ማእከል ውስጥ

​ስለ ኻሜኒ እንቅስቃሴ እንዲህ ያለ ወሳኝ መረጃ ሊሰጥ የሚችለው ማን ነው? የሚለው ዋነኛው ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል። በወሬዎች መሀል ስማቸው እየተነሳ ያለው የአብዮታዊ ጥበቃ የቁድስ ሃይል አዛዥ ጄኔራል እስማኢል ቃአኒ ናቸው። የቃሲም ሶሌይማኒ ተተኪ የሆኑት ቃአኒ፣ የኻሜኒ የቅርብ ረዳት እና የኢራን የውጭ ኦፕሬሽኖች ቁልፍ መሪ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር።

​የሳቸው ስም መነሳቱ እና የሞሳድ መረጃ ሰጪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ግምት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፣ በተከታታይ በተከሰቱ አጋጣሚዎች ላይ የተመሰረተ ነው። ቀደም ባሉት የእስራኤል ጥቃቶች (በኢራን ውስጥም ሆነ በሊባኖስ) ቃአኒ ጥቃቶቹ ከመፈፀማቸው ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ እንደወጡ ይነገራል።

የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ በተገደለበት ወቅት ቃአኒ በዚያው አካባቢ ቢኖሩም ሳይመቱ መቅረታቸው ነው።

​ይህ መረጃ በቴህራን ውስጥ ጥርጣሬን የጨመረ ሲሆን፣ መረጃው ከከፍተኛ ወታደራዊ አመራር ደረጃ ሊሾልክ እንደሚችል ግምቶችን አቀጣጥሏል። ጄኔራሉ በቁጥጥር ስር ውለው ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸው የሚገልጹ ዘገባዎች ሲሰራጩ ወሬው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ምንም እንኳን ይፋዊ ማረጋገጫ ባይኖርም፣ ስማቸው በየዋና ዋና ኦፕሬሽኖች ላይ በተደጋጋሚ መነሳቱ ከፍተኛ ያለመተማመን መንፈስ ፈጥሯል።

​በኤክስ (X) ማህበራዊ ገጽ ላይ ደግሞ ጉዳዩ የፌዝ መልክ ይዟል፤ ተጠቃሚዎች የሞሳድ ሰርጎ ገብነት በጣም ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ስለ ዋና ተዋናዮቹ እውነተኛ ማንነት እርግጠኛ መሆን አይችልም በማለት እያፌዙ ይገኛሉ።

​ከጥቃቱ በስተጀርባ ያለው መልእክት

​ከግለሰቦቹ ባለፈ፣ ዋናው ጉዳይ የግጭቱን ባህሪ ይመለከታል። በእርግጥ ሞሳድ በጥቃቱ ወቅት ኻሜኒ የት ተቀምጠው እንደነበር እንኳ የሚያውቅ ከሆነ፣ ድርጊቱ ከወታደራዊ እርምጃ በላይ ነው። ይህም በመረጃ እና በስነ-ልቦና ጦርነት ረገድ ያለውን ስትራቴጂያዊ የበላይነት የሚያሳይ መልእክት ነው።

​አንድ የውጭ የስለላ ድርጅት በዓለም ላይ ካሉ በጣም ዝግ የፖለቲካ መዋቅሮች የአንዱን ውስጣዊ ሂደት እንዲህ በጥንቃቄ መለየት መቻሉ፣ ለኢራን አገዛዝ ትልቅ የታማኝነት ውድቀት ከመሆኑም በላይ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የሃይል ፍልሚያ መልክ የሚቀይር ነው።
7 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.