Logo
FastMereja
በመስኮት በመግባት ከ6 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶችን ሰርቋል ተብሎ የተጠረጠረን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

ጌቱ ተስፋዬ የተባለው ተጠርጣሪ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመው የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሳፋየር አዲስ ሆቴል አካባቢ ከሚገኝ አንድ አፓርትመንት 8ኛ ፎቅ ከምሽቱ 5፡00 ገደማ ነው።

ተጠርጣሪው በአፓርታማው ከሚገኝ አንድ ሬስቶራንት በአስተናጋጅነት የሚሰራ ሲሆን የግል ተበዳይ ወይዘሪት እልፍነሽ አሰፋ የመኝታ ክፍል መስኮት አለመዘጋቱን በማረጋገጥ ከወርቅና ከዳይመንድ የተሰሩ ልዩ ልዩ የአንገት ሀብል፣ የጣት ቀለበት፣ የእጅ ብራስሌትና የጆሮ ጌጣጌጦች፣ 2800 የአሜሪካ ዶላር፣ 2 ሞባይል ስልኮችና የተለያዩ ጌጣጌጦችን በመኝታ በኩል በሚገኝ መስኮት ዘሎ በመግባት የስርቆት ወንጀሉን ፈፅሞ ከአካባቢው ይሰወራል፡፡

የየግል ተበዳይ ወይዘሪት እልፍነሽ አሰፋን አቤቱታ የተቀበለው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ፖሊስ ጣቢያም የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት ለማረጋገጥ ህንፃው ላይ በተገጠመው የደህንነት ካሜራ (CC TV) አማካኝነት በማረጋገጥና ክትትል በማድረግ ግለሰቡ ለጊዜው ተሰውሮ ከነበረበት ሜክስኮ አካባቢ ከሚገኝ አልጋ ቤት ከነ ንብረቶቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን ከአደይ አበባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ማምለጥ እንዳማይችል የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ህብረተሰቡ በመኖሪያ ቤቱም ሆነ የሚያርፍባቸው ቦታዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን በሚገባ ማረጋገጥ እንደሚገባም ጭምር መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

4 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.