Logo
Getu Temesgen
አዝማች ይርጋ ገብሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

አዝማች ይርጋ ገብሬ ትውልድ እና እድገታቸው አዲስ አበባ ሲሆን ባለ ትዳር እና የአራት ልጆች አባት ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቀድሞ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ዪኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሀገረ አሜሪካ ተከታትለዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይም ዲፕሎማዎችን እና እውቅናዎችን አግኝተዋል፡፡

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እና በባህር ማዶ በመዘዋወር በመምህርነት እና ተዛማጅ ዘርፎች እንዲሁም በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ጥንቅቅ ያሉ ተመራማሪ፣ ባለሙያ እና መሪ ነበሩ፡፡

በጠቅላይ ሚንስቴር ቢሮ የኦዲት እና ኡንስቴክሽን ሀላፊ፣ በጉራጌ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ከአባልነት እስከ ከፍተኛ አመራር ሆነው አገልግለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም ሰላም ለመፍጠር የሚያስችሉ ምርምሮችና ጥናት ማካሔድ እና ማማከር፣ በአለም ባንክ ፋይናንስ ለተደረጉ የጤና፣ የትምህርት፣የኤች. አይ.ቪ ኤድስ ፕሮጀክቶች ጥናት ማካሔድ እና ማማከር እንዲሁም ከ13 በላይ ሀገራዊ ተቋማት ላይ በስራ አስፈጻሚነት፣ በቦርድ ሰብሳቢነት እና በአማካሪነት መስራታቸው ብቻ ለአብነት የሚጠቀሱ ነው፡፡

በሀገራችን የኢኮኖሚው ዘርፍ በዘመናዊ መንገድ እንዲመራ እና ስኬታማ በሆኑ ግዙፍ አክሲዎኖች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆንም ይታወቃሉ፡፡ ለአብነትም አልፋ ትምህርት እና ስልጠናዎች አክሲዮን ማህበር፣ አልፋ አታሚዎች፣ ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ንብ ባንክ እና ንብ ኢንሹራንስ ውስጥ ያላቸው ሚና እጅግ ግዙፍ ነው፡፡

ባለ ብዙ መልክ የሆኑት አባት እድሜ ልካቸውን ያገለገሉዋት ሰፊውን ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን ከምንጩ ለተቀዱበት የጉራጌ ማህበረሰብም ብዙ ብዙ ግልጋሎቶችን ሰጥተዋል፡፡

በመብት ትግል ውስጥ በደርግም ሆነ በኢሀዲግ መንበረ ስልጣን ውስጥ የማህበረሰቡ መብቶች እንዲከበሩለት ፊት ለፊት ተጋፍጠዋል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጲያ የጎልማሶች ትምህርት መምሪያ በነበሩበት ወቅት ለጉራግኛ ቋንቋ ፊደል ቀረጻ እና በጉራግኛ ቋንቋ መጽሐፍት እንዲታተሙ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የስዊድን ተራድኦ ድርጅት በማስተባበር የቋንጤ ትምህርት ሲመሰረት የእሳቸው ጥረት ፍሬ አፍርቷል፡፡ የሙጎ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምስረታ እና የጉፐና ትምህርት ቤት በአዲስ መልክ ሲደራጅ በገንዘብ በእውቀት እና የአመራርነት ሚና በመውሰድ ለአካባቢው ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ፈር ቀዳጅ ሆነዋል፡፡

እንዲሁም ጉርዳ ሊንክ በተባለ ድርጅት ባህር ማዶ በሚኖሩ የቤተ ጉራጌ ተወላጆች በአሜሪካ አቋቁመው በጉራጌ ዞን እና በሌሎች አካባቢዎች ልዩ ፍላጎት ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች አዳሪ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ሚያስችል ፕሮጀክት ለማስፈጸም በኢትዮጲያ ተወካይ እና ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን ሰርተዋል፡፡

በተጨማሪም በባህላዊ የግጭት አፈታት ስርአት በመጠቀም ብዙ ችግሮችን መቅረፋቸውን እና እየቀረፉ በመሆኑ ለሀገራችን የሽምግልና ስርአት ሞዴል ናቸው፡፡

የጆካ ቂጫ ወደ ጹሁፍ ህግ ሲቀየር ንቁ ተሳታፉ የነበሩ እና የጉራጌ ባህል ማእከል እና የጉራጌ መንገድ ስራ ድርጅትን ከመሠረቱና ከመሩ ሰዎች መሀከልም አንደኛው ናቸው፡፡ በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለአስተዳደር ስራዎች ምቹ ሲደረግ የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡

የጉራጌ አባት፣ ነገር አዋቂ፣ አንደበተ ዕርቱው፣ የሀገር ሽማግሌ፣ በተለያዩ ተቋማት አንቱታን ያተረፉ ባለሙያ፣ ህግ አዋቂ እና በተለያየ የልማት ስራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እና መሪ የሆኑት አዝማች ይርጋ የፖለቲካ ተሳትፎዋቸውም የሚደንቅ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ፣ ጉህዴግ፣ በቅንጅት እና ኢዜማ ውስጥ በመሳተፍ ለሀገራችን ዲሞክራሲያዊ እድገት በሰላማዊ መንገዶች እንዲመጣ ብዙ ጥረዋል፡፡

አዝማች ይርጋ ገብሬ በአደባባይ ሰውነታቸው የሰሩትን ስራ ብቻ ሳይሆን የሚደነቀው የሚኖሩበት መንደር እና ቀዬ ውስጥ (አዲስ አበባ ጌጃ ሰፈር ውስጥ ባሉ መንደሮች) መኖርያ መንደሩ ምቹ ለማድረግ በውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ በሰላም እና ደህንነት፣ በጤናና እና ማህበራዊ ዘርፎች ማን እንደሳቸው የተባለላቸው የህዝብ አገልጋይ ነበሩ፡፡

ለመላው የጉራጌ ህዝብ መፅናናትን እንመኛለን 😭

ነፍስ ይማር

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር - International Gurage Association - IGA

5 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.