Logo
FIDEL POST NEWS
​የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ሀገራቸው የሩሲያዊው ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪች የቼልሲ እግር ኳስ ክለብን በመሸጥ ካገኙት ገንዘብ ውስጥ 2.5 ቢሊዮን ፓውንድ ለዩክሬን የሰብአዊ እርዳታ ፈንድ እንደምታስተላልፍ 'ዘ ጋርዲያን' ዘግቧል።

​ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር በብሪታንያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፦ "እ.ኤ.አ. በ2022 ታግዶ የነበረውን የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ሽያጭ ገቢ 2.5 ቢሊዮን ፓውንድ እንዲተላለፍ ፈቃድ መስጠታችንን ማብሰር እፈልጋለሁ። ለአብራሞቪች ያለኝ መልዕክት ግን ይህ ነው፦ ጊዜው እያለቀ ነው፤ የገባኸውን ቃል አክብርና አሁኑኑ ክፈል" ብለዋል።

​አክለውም አብራሞቪች ለመክፈል ፈቃደኛ ካልሆነ የብሪታንያ መንግስት "ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ" ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

​"በፑቲን ህገ-ወጥ ጦርነት ህይወታቸው ለተመሰቃቀለባቸው ወገኖች እያንዳንዱ ሳንቲም መድረሱን ለማረጋገጥ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ለመሄድ ዝግጁ ነን" ብለዋል ስታርመር።

​የቀድሞው የሩሲያ የቹኮትካ ክልል ገዥ የነበሩት አብራሞቪች፤ የሩሲያ የዩክሬ ግጭት ተከትሎ ከብሪታንያ መንግስት በደረሰባቸው ጫና ምክንያት የቼልሲ እግር ኳስ ክለብን በ2022 መሸጣቸው ይታወሳል።
​በወቅቱ ሽያጩን እንዲያካሂዱ ከብሪታንያ መንግስት ፈቃድ ያገኙት፤ ከሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ በሩሲያ ወረራ ለተጎዱ ሰለባዎች መርጃ እንዲውል በሚል ቅድመ ሁኔታ ነበር።

​የሽያጭ ገቢው ፎርድስታም በተሰኘው የአብራሞቪች ኩባንያ በሚተዳደር የብሪታንያ ባንክ ሂሳብ ውስጥ ይገኛል።

​ገንዘቡ እስካሁን ታግዶ የቆየው፤ "ገንዘቡ ለዩክሬን እርዳታ ብቻ ይዋል ወይስ በሌሎች ሀገራትም ለሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታዎች ይዋል?" በሚለው ጉዳይ ላይ ከአብራሞቪች ጋር ስምምነት ላይ ባለመደረሱ እንደሆነ ተጠቁሟል።
10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.