Logo
YenetaTube
የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ያጠናከረ ግኝት ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ያጠናከረ ግኝት በአፋር ክልል በጎና መካነ ቅርስ ሥፍራ መገኘቱ ይፋ ሆኗል፡፡

አዲሱ ግኝት በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የጎና የአርኪዮሎጂ የምርምር ጥናት ተመራማሪ በሆኑት በስለሺ ሰማው (ዶ/ር) እና ሮጀርስ ማይክል (ዶ/ር) መሪነት የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ግኝቱን አስመልክተው የጎና የቅርስ መካነ ጥናት መሪ እንዲሁም በስፒን የሰው ዘር አመጣጥ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና ሳይንቲስት የሆኑት ስለሺ ሰማው (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም፤ በጎና መካነ ጥናት የተገኘው 1.5 ሚሊዮን ዓመታት እንደሚደርስ የተገመተው ሆሞ ኢሬክተስ በመባል የሚታወቀው የቅድመ ሰው ዝርያ ጭንቅላትና ፊት በቨርቹዋል ዲጂታል ሪኮንስትራክሽን በሳይንቲስቶች መጠናቱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ቀደምት የሰው ዝርያዎች ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ እና እስያ አህጉራት ያደረጉትን እንቅስቃሴና ኦልድዋን እና አሹሊያ በመባል በሚታወቁ የድንጋይ መሳሪያ መጠቀማቸውን በተመለከተ አዲስ መረጃ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

አዲሱ ግኝት በአፍሪካ እስካሁን ይፋ ከሆኑ ተቀራራቢ እድሜ ካላቸው ግኝቶች የመጀመሪያው የራስ ቅል እና የፊት አጥንቶችን (ጥርሶችን ጨምሮ) የሚያሳይ መሆኑን በቨርቹዋል ዲጂታል ሪኮንስትራክሽን ዘዴ ለማየት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የጥናቱን ውጤት አስመልክተውም የራስ ቅሉና የፊቱ ቅርፅ ከ300 ሺህ ዓመታት በፊት እድሚያቸው 1.8 ሚሊዮን ዓመታት የሚገመቱና ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካን ለቀው ወደ አውሮፓና እስያ ከፈለሱት የቅድመ ሰው ዝርያዎች የጭንቅላትና የፊት ገፅታ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውም ተናግረዋል ፡፡

አዲሱ ግኝት ሳይንቲስቶች ከ1.8 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ወደ አውሮፓና እስያ የፈለሰውን የቅድመ ሰው ዝርያ ከጊዜ በኋላ ከኤስያ ወደ አፍሪካ ተመልሷል የሚለውን መላምት ውድቅ ደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሆሞ ኢሬክተስ በአፍሪካ ውስጥ በአዝጋሚ ለውጥ የአሁኑ የሰው ዘር ግንድ መሆኑን ያሳየና ኢትዮጵያም የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚያጠናክር ግኝት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሳይንቲስቱ አክለውም የሆሞ ኢሬክተስ ዝርያ ቀደምት የሆነና ኦልድዋን እና አሹሊያ በመባል በሚታወቁ የድንጋይ መሳሪያ መጠቀሙ ዝርያውን ልዩ እንደሚያደርገውና የነዚህ የሁለቱ የድንጋይ መሳሪያዎች ከሆሞ ኢሬክተስ ጋር ባንድ ላይ መገኘታቸው በአርኪዎሎጂ ጥናት እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ የጎናውን ግኝት አስደናቂ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

የቨርቹዋል ሪኮንስትራክሽን ስራ ከዓመት በላይ ጊዜ እንደወሰደባቸው፣ የተገኘው የራስ ቅልና ፊት ከሌሎች ተመሳሳይ እድሜ ካላቸው የቅድመ ሰው ዝርያዎች የአንጎሉ መጠን አነስተኛ መሆኑን እንዲሁም በጥናቱ ከ300 ሺህ ዓመታት በፊት ከነበሩ ሆሞ ሀቢሊስ በመባል ከሚታወቁት የቅድመ ሰው ዘር ዝርያ ጋር መመሳሰሉን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ከአፍሪካ ቀደም ሲል ከ1.8 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ከፈለሱት የቅድመ ሰው ዝርያዎች የፊት ገፅታን ይዞ ሳይለወጥ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

እስካሁን በጎና እና በመካከለኛው አዋሽ የጥናት ፕሮጀክቶች የተገኙ የቅድመ ግኝት የሰው ልጅ ዝርያዎች፣ ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ቅርሶች ቀዳሚ አድርጓታል ተብሏል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ለመሆኗ ጉልህ ማረጋገጫ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
#ebc

6 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.