Logo
Getu Temesgen
"ግንባታ ለበዓታ"

📍አጠቃላይ ግንባታው ሁለት ቢሊዮን ብር ይፈጃል
#ethiopia | ለ93 ዓመታት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ሲያገለግል የቆየውና በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ያፈራው የታዕካ ነገሥታት በዐታ ለማርያም ገዳም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና የቀሳውስት ማሠልጠኛ አዳሪ፣ መንፈሳዊ አብነት ትምህርት ቤት አዲስ ግንባታ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አሳወቀ።

የገዳሙ ሰበካ ጉባዔ መንፈሳዊ አስተዳደር የልማት ኮሚቴ ባቋቋመው ዝግጅት መሠረት፣ ለግንባታው የሚያስፈልገው የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ፣ ዛሬ ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በአንጋፋው ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም አዳራሽ፣ ከዲዛይን ጨረታው አሸናፊ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

የልማት ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ በጨረታው ከተወዳደሩ 10 ተጫራቾች መካከል ኢሜጅ ኮንሰልቲንግ የተባለው ድርጅት በ1,623,800 ብር አሸናፊ በመሆን ከገዳሙ አስተዳደር ጋር ውል ተፈራርሟል።

ከስምምነቱ ፊርማ ባሻገር "ግንባታ ለበዓታ" በሚል መሪ ቃል፣ ከኅዳር 27 እስከ ታኅሣሥ 3 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ልዩ የገንዘብና የቁሳቁስ ማሰባሰቢያ የሚዲያ ቅስቀሳ መርሐ ግብር እንደሚካሄድ በዛሬው እለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ገዳሙ በምትክ በተሰጠው 10,248 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሊያከናውናቸው ያቀዳቸው ግንባታዎች መካከል
የአብነት ትምህርት ቤት መማሪያ ህንጻዎች ፣የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት ማደሪያ ፣ የአባቶች መነኮሳት እና አገልጋዮች ማደሪያ ፣ የአስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ የተማሪዎች መመገቢያ ፣ የገዳሙ አረጋዊያንና ዕጓለማውታ ማረፊያ ቤት፣ ለገቢ ማስገኛ የሚኾኑ ቢሮና ሱቆችን ያካተተ እንደሆነ አጠቃላይ ግንባታው ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ ገልጸዋል።

ለበአታ ግንባታ ሥራ የገንዘብ ገቢ ማሰባሰቢያ ሂሳብ ቁጥር፡-
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
1000180583932
1000010836097

ሎዛ ኹነቶች ባስተባበረው ጋዜጣዊ መግለጫ መርሐግብር ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፣የአብነት ትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

10 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.