Logo
YenetaTube
በሰንበት ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከመደበኛ የገበያ ሽያጭ ዋጋ አንፃር ልዩነት እንደሌላቸውና የጥራት ጉድለት እንዳለባቸው ሸማቾች ቅሬታቸውን ገለጹ

በአዲስ አበባ ከተማ በሰንበት ገበያ ማዕከላት የሚቀርቡ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና ምርቶች ከመደበኛ ገበያ የሽያጭ ዋጋ አንፃር ምንም አይነት ልዩነት እንደሌላቸውና ምርቶቹ ጥራታቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው ምክንያት ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገናል ሲሉ ሸማቾች ቅሬታቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።

በተቋቋሙ ገበያ ማዕከላት ውስጥ ምርቶችን የሚሸጡ ነጋዴዎች የሚያቀርቧቸው ግብዓቶች፤ በተለጠፈው ዋጋ አማካኝነት እንደማይሸጡላቸውና በተለይ የግብርና ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

አንዳንድ ምርቶች ከመደበኛ ገበያ ዋጋ አንፃር ከፍ እንደሚሉ የገለጹም ሲሆን፤ በተለጠፉ የዋጋ ተመን ነጋዴዎች እንደማይሸጡላቸው አክለዋል።

በተጨማሪም ምርቶችን ከገዟቸው በኋላ በጥራት ጉድለት ምክንያት እንደሚጥሏቸው ተናግረዋል።

መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማጣጣም እና የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ታቅደው እንዲሁም ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አምራች ና ሸማችን በቀጥታ እንዲያስችለው ታስበው የተቋቋሙ ማዕከላቱ ውስጥ ሕገ-ወጥ ተግባራት እንደሚያጋጥሟቸው ነዋሪዎች አሳስበዋል። በዚህም ምክንያት ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገናል ብለዋል።

አሐዱም የነዋሪዎቹን ቅሬታ በመያዝ፤ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮን አነጋግሯል።

የቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሀኑ በምላሻቸውም፤ በሰንበት ገበያ ማዕከላት ከተለጠፈው ዋጋ ውጭ ምርቶችን በሸጡ ከ13 በላይ ነጋዴዎች አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ የሰንበት ገበያ ማዕከላት መቋቋም አላማን ሲያስረዱ፤ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የዜጎችን የምርቶች ፍላጎትን ከአቅርቦት ጋር ለማጣጣም እንደሆነ ነው።

ከጥራት አኳያ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና ምርቶች የግብይት የጥራት ፕሮሞሽን የዋጋ የምርት ጥናት ይካሄዳል ያሉም ሲሆን በጥናቱ መሰረት ግብይት እንደሚደርግ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የዋጋና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎች በምርቶች ላይ ይካሄዳል ብለዋል። የተወሰዱ እርምጃዎች የጹሑፍ እና የማስጠንቀቂያ እንደሆነም ነግረውናል።

ከሰንበት የገበያ ማዕከላት ጋር በተገናኘ ነዋሪዎች የሚቀርቡላቸው ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ አቤቱታዎችን ሲያሰሙ ይደመጣል።
#አሐዱ

11 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.