Logo
YenetaTube
ካልተሳሳትኩ 2010 ዓ.ም. ላይ ወደ ጎንደር ሊቃውንት የተገኙበት የወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ውይይት ላይ ከመምህር ያረጋል አበጋዝ ጋር ለማገልገል ሔደን ነበር:: በጉባኤው ፍጻሜ ላይ ሊቃውንቱ የሞቀ ውይይት ሲያደርጉ ከተሳታፊዎች መካከል አንድ እንደ ነገሩ ነጠላ ጣል ያደረገ ልጅ እግር ተማሪ ሃሳብ ሊሠጥ ተነሣ:: በጣም ጥልቅና ብስለት የተሞላበት በፍጹም መንፈሳዊነት የተዋበ አስተያየት ሰጥቶ ቁጭ አለ:: በንግግሩ ጥራት በሃሳቡ ጥልቀት ተደንቄ ቀስ ብዬ ወደ መምህር ያረጋል ዞር ብዬ "እንዴት የሚገርም ሊቅ ነው?" ብዬ በሹክሹክታ ላደንቅ ስል "ኸረ የሊቀ ሊቃውንት ምክትል እኮ ናቸው:: የኔታ በጽሐ ማለት እርሳቸው ናቸው" አለኝ:: ክው!

ሊቃውንት ካባ ላንቃ ሳይደርቡ መነሳንስ ሳይይዙ የሚናገሩት ንግግርና መንፈሳዊነታቸው ብቻውን ልብስ ሆኖ ተራ ሰው አለመሆናቸውን ያሳብቃል:: የኔታ በጽሐ በዚያች ቀን ያደረጓት ነጠላ እስክትጨነቅ ድረስ የተናገሩት ጥበብ የተሞላ ንግግር የሚያንቀጠቅጥ ነበረ:: ያን ቀን በሩቅ አይቼ የረቀቁብኝን እኚህን ሊቅ ከዚያ ወዲያ ደጋግሜ የማግኘትና እንደ ቅርብ ወዳጅ የማዋየት ዕድል ገጥሞኝ ብዙ ብዙ አሳልፈናል:: እውነት ለመናገር ቤተ ክርስቲያን "ዘልብየ በጽሐ" (የልቤ ደረሰ) የምትልላቸው እጅግ ድንቅ ሊቅ ናቸው::

መቼም በረባ ባልረባው መመሰጋገን ተለመደና አመስጋኝ ሁሉ አድርባይ መስሎ ታየ እንጂ ስለየኔታ በጽሐ የምለው ብዙ ነበር:: መምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ ትሕትናቸው እንኳንስ ሊቅ ፊደል እንኳን የቆጠሩ አያስመስላቸውም:: ምሥጢር በሚገባ ያደላደሉ የመጻሕፍት መምህራንን ትሕትና መቼስ ታውቁታላችሁ:: የመጻሕፍት መምህራን የርግብ የዋህነት ፣ የዕባብ ብልህነት ፣ የንስር ተመስጦ ያላቸው ቃለ እግዚአብሔር እንደ ሕፃን ያደረጋቸው ትሑታን ናቸው::

መምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ እንግዲህ ምድባቸው ከእነዚህ ሊቃውንት ጋር ነው:: ትሕትናቸው የሚያስጨንቅ ፣ በዕውቀታቸው ጥምጥምን ያስከበሩ ፣ እንደ ብስለታቸው ልክ ቢጠመጥሙ ኖሮ ተራራ ቢሸከሙ የማያንሳቸው ሊቅ ናቸው::

የታዖዶኮስ (ወላዲተ አምላክ) የፍቅርዋ እስረኛ ፣ ቤተ ክርስቲያንን በዘባነ ሕሊናቸው ተሸክመው ጉባኤ ቤትዋን እንደ መሠዊያ ዐጥነው የሚኖሩ ፣ ለአብነት ትምህርት ማደሪያ እስኪያገኙ ድረስ ለዓይናቸው እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቻቸው ዕረፍትን የማይሠጡ የሊቃውንት ምሳሌ ናቸው:: ጉባኤ ቤት ከየትኛውም ዩኒቨርስቲ የማይተናነስ ሆኖ እንዲደራጅ ፣ ጉባኤ ቤት የገባ ደቀ መዝሙር ዳግም ሌላ የትም ትምህርት ቤት መግባት የማያስፈልገው ሁለገብ ሰባኪ አስተዳዳሪ ጸሐፊ አመስጣሪ መሪ ሆኖ እንዲወጣ የሚንከራተቱ ፣ ተማሪዎቻቸውን ቀለም እያስቆጠሩ እርሳቸው በጭንቀት ብሎኬት የሚቆጥሩና የትምህርት ቤቱ ግንባታ ዕረፍት የነሣቸው ልብ የሚነካ መንፈሳዊ ቅናትና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያን ያቃጠላቸው መምህር ናቸው::

የየኔታ በጽሐ የልቡና ስፍሐት ያስደንቀኛል:: መጻሕፍትን የሸመደዱ ሳይሆን በደንብ ያላመጡ ስለሆኑ ከምናውቀው መጽሐፍ ውስጥ ያላየነውን ማሳየት የሚችሉ ናቸው:: ስለ ንዑሰ ክርስቲያን አገልግሎት ያላቸው ጭንቀት ፣ ስለ ምእመናን ሕይወት ያላቸው መሳሳት ፣ ከወጣቱ ትውልድ ጋር ያላቸው ቅርበትና ለድካም መራራት ለማመን የሚያስቸግር ነው:: የጥንት መምህራንን ማንነት ገና መጪውን ዘመን ከሚዋጅ አርቆ አሳቢነት ጋር የሚታየው እርሳቸው ጋር ነው::

ሰሞኑን የኔታ በጽሐ ለጉባኤ ቤታቸው ማስፈጸሚያ ደጅ ሊጠኑ ጉባኤውን ትተው ቅስቀሳ ጀምረዋል:: በእውነት ተንከራትተው የተማሩትን ሊቅ ተንከራትተው እንዲያስተምሩ አድርገን ግፍ አንሥራ::
እንዳያስፈርዱብን የሚቻለንን በሚከተሉት የባንክ ቁጥሮች እንርዳና ወደሚወዱት ጉባኤያቸው በቶሎ እንመልሳቸው::

የደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት የምስክር ጉባኤ ቤት

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000727772727
ዓባይ ባንክ 4659412373459012
አማራ ባንክ 9900045603575
አሐዱ ባንክ 0018263111702
አዋሽ ባንክ 013521664644700
አቢሲኒያ ባንክ 208943774

USD / ዶላር አካውንት
1000725696055

Euro / ዩሮ አካውንት
1000725696586

ለበለጠ መረጃ
0918523699
0918062008

12 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.