Logo
FastMereja
ከደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የ፬ቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

“ከአባቶቻችን ለልጆቻችን!” ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ የደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የ፬ቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት “በኦርቶዶክሳዊ ትውፊትና ትምህርት ዓለም አቀፍ በጎ ተጽዕኖ በመፍጠር ትውልድ አሻጋሪ የልሕቀት ጉባኤ ቤት መሆን” የሚለውን ራዕይ ለማሳካት ወሳኝ ዓለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ጥቅምት-16-2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ እንደሚያዘጋጅ በታላቅ ክብር ይፋ ያደርጋል።

የዚህ ጉባኤ ዋነኛ ዓላማው ለጉባኤ ቤቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተለይም ለB+G+4 ዓለም አቀፍ (ኢንተርናሽናል ስኮላርሽፕ) መንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል ግንባታ የሚያስፈልገውን 72 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ነው። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት የጉባኤ ቤቱን ራዕይ እውን ለማድረግ ወሳኝ ምሰሶ ሲሆን፣ ለትውልዱ መንፈሳዊ እና አካዳሚያዊ ልህቀት በሩን ይከፍታል።

በጉባኤ ቤቱ የሚሰራው ይህ ዓለም አቀፍ የትምህርት ማዕከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጥልቅ እና ረቂቅ ትውፊትና መንፈሳዊ ትምህርት ለዓለም ለማካፈል ያለመ ነው።

በመሆኑም ማዕከሉ የሚከተሉትን ቁልፍ ዓላማዎች አንግቧል፦
ዓለም አቀፍ የስኮላርሽፕ ፕሮግራም: ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ደቀመዛሙርት በስኮላርሽፕ ላይ የተመሠረተ ጥልቅ መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጣል።

ደቀመዛሙርቱ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ ትምህርትና ትውፊት ከምንጩ ቀስመው ካጠናቀቁ በኋላ ወደየሀገራቸው ተመልሰው ቤተክርስቲያንን በብቃት እና በመንፈሳዊነት እንዲያገለግሉ ለማብቃት ያለመ ነው።

ተጨማሪ የማብቂያ ትምህርት: በአገር ውስጥ ከተለያዩ የዜማ ትምህርት ቤቶች (ድጓ፣ ተክሌ፣ ዝማሬ መዋስዕት …) ተምረው ያስመሰከሩ ሊቃውንት የወንጌልን ትምህርት በብቃት ማስተማር እንዲችሉ ተጨማሪ የማብቂያ ትምህርት ይሰጥበታል።

ትምህርትና ስልጠና፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በሀገር ውጭ ለሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ወጣቶች፣ ካህናት እና የአብነት መምህራን አጫጭር ስልጠናዎች የሚሰጥበት ማእከል ይሆናል፡፡

የልምድ ልውውጥ መድረክ: የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የክርስትና አስተምህሮ ልምድ የሚቀሰምበት፣ ሊቃውንቱና እና ምሁራኑ እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት ማዕከል ይሆናል።

የእንግዳ ማረፊያ: አበው ጳጳሳትና መምሀራንን ለማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ማረፊያ ይኖረዋል።

ታሪክንና ባህልን ማስተዋወቅ፡ ይህ ማዕከል በሀገሪቱ የሚገኙ ልዩ ልዩ ቅርሶችንና መንፈሳዊ ሀብቶችን በአንድ ማዕከል በማደራጀት ትውልዱ እንዲማርባቸውና እንዲያውቃቸው የሚያስችል ክፍል ይኖረዋል፡፡

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ጉባኤ ቤቱ ግንባታውን ለማስቀጠል የሚያስችል በቂ ገንዘብ የሌለው በመሆኑ የዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ስኬታማነት ለፕሮጀክቱ ቀጣይነትና ለጉባኤ ቤቱ ዓለም አቀፍ ራዕይ መሳካት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል። እያንዳንዱ አስተዋጽኦ ለዘመናት የሚሻገር መንፈሳዊ ቅርስ በመገንባት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ብርሃን ለዓለም በማብራት እና ትውልድን በእውቀትና በመንፈሳዊነት በመገንባት ታላቅ እገዛ ያደርጋል።

ደብረ ታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የ፬ቱ ጉባኤያት ምስክር ጉባኤ ቤት ይህንን ታላቅ ዓላማ ለማሳካት የመላው ምእመናን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የመንግስት አካላት እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ልባዊ ድጋፍ በአክብሮት ይጠይቃል። ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ “ከአባቶቻችን ለልጆቻችን!” የሚለውን መርህ በመከተል፣ የቤተክርስቲያንን ቅርስ በመጠበቅ እና ለትውልድ በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ የሁላችንንም ተሳትፎ ይጠይቃል።

በመሆኑም ሁላችሁንም በጥቅምት 16 ቀን 2018 ዓ.ም (October 26, 2025) በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንድትሳተፉ ጥሪ እያስተላለፍን።

12 months ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.