Logo
Getu Temesgen
የህዝብ ክብረ በዓላትን ለማስተዋወቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
#ethiopia | የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልማህዲ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የህዝብ ክብረ በዓላትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታዋ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለዘመናት የዳበሩ እና በትውልድ ቅብብሎሽ የጎለበቱ እምቅ የባህል ሀብቶች ባለቤት ነች። እነዚህን ሀብቶች በመጠቀም ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ባህል ለማህበረ-ኢኮኖሚ እድገት ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሚኒስቴሩ በፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ሰፊ ስራ እየሰራ ነው።

በመግለጫቸው፣ በመጪዎቹ ሶስት ወራት የተለያዩ የህዝብ በዓላት እንዲከበሩ የባህል ንቅናቄ መጀመሩን አስታውቀዋል። ይህ ንቅናቄ ከፌደራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በቅንጅት የሚከናወን ሲሆን፣ የህዝብ ተሳትፎን በማሳደግ የጋራ እሴቶችን ለማጎልበት ያለመ ነው።

በ2018 በጀት ዓመት የአዲስ ዓመት አቀባበል እና የጳጉሜ ቀናት በኪነ-ጥበብ ስራዎችና የተጎዱ ዜጎችን በመርዳት የመተሳሰብ እና የአብሮነት ባህላችንን በማጎልበት መከበራቸውን ወ/ሮ ነፊሳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ክልሎች የተከበሩ የባህል በዓላትን በመጥቀስ፣ በትግራይ አሸንዳ፣ በአማራ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ለቀማና ቡሄ፣ በኦሮሚያ ጎቤ እና ሽኖዬ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጉዋንዳ፣ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የዳውሮ ቶኢ-ቤኣ እና የኮንታ እንግጫ ክብረ በዓላት በደመቀ ሁኔታ መከበራቸውን አብራርተዋል።

በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላትን በተመለከተም መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በደቡብ ኢትዮጵያ የጊፋታ፣ የዮ መስቀላ እና የጋዜ መስቀላ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የማሳላ፣ ያሆደ፣ መስቀል እና ሄቦ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ማሽቃሮ ባሮ፣ በኦሮሚያ ኢሬቻ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋሪ ዎሮ ክብረ በዓላት በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በመጨረሻም፣ እነዚህ በዓላት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጠናክሩ በመሆናቸው፣ ህዝብና መንግስት በጋራ ተቀናጅተው የተሳካ በዓል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። እንዲሁም፣ ሚዲያዎች እነዚህን በዓላት በአገር አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ አገራዊ ገፅታን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አሳስበዋል።

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.