Logo
Getu Temesgen
ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በተደጋጋሚ በመዝጋት በአፍሪካ ቀዳሚ ናት - ጥናት

#ethiopia | ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በተደጋጋሚ በመዝጋትና የኢንተርኔትን ነጸነት በመገደብ ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን በብሉምስበሪ አሳታሚ የታተመ ጥናት አመለከተ።

“የኢንተርኔት መዘጋት በአፍሪካ” በሚል ርእስ በፊሊሽያ አንቶኒዮ እና ቶኒ ሮበርትስ የተጠናውና መቀመጫውን በእንግሊዝ ባደረገው ብሉምስበሪ አሳታሚ ድርጅት በመጸሐፍ መልክ ታትሞ የወጣው ጥናት፣ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2024 በአህጉረ አፍሪካ በሀገራት የተፈጸመውን የኢንተርኔት መዘጋት ገምግሟል።

በዚህም ከ2016 እስከ 2024 ባሉት በለፉት ዘጠኝ ዓመታት 193 የኢንተርኔት መዘጋቶች በአፍሪካ አህጉር መመዝገቡን ገልጿል።

በተጠቀሱት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በተፈጸሙ የኢንተርኔት መዘጋት ድግግሞሽ መጠኖች ሀገራትን በደረጃ ያስቀመጠው ጥናቱ፤ ኢትዮጵያን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሰላሳ ጊዜ ኢንተርኔት የዘጋች በሚል፣ ከ55ቱ የአፍሪካ ሀገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኘው ጎረቤት ሀገር ሱዳን፣ በተጠቀሱት ዓመታት 21 ጊዜ ኢንተርኔትን በመዝጋት በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ስትቀመጥ፤ ባለፉት ዓመታት በሰላም እጦትና በግጭት ውስጥ ያለችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጀሪያ ደግሞ 14 ጊዜ ኢንተርኔትን በመዝጋት በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአህጉሪቱ የተፈጸመው የኢንተርኔት መዘጋት ሁኔታና የድግግሞሽ መጠኑ ከሀገር ሀገር ከፍተኛ ልዩነት የሚታይበት መሆኑንም የጥናቱ ውጤት አመላክቷል። በዚህም ምንም እንኳን በብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት መዘጋት የነበረ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ በዚያው ልክ ደግሞ በ14 የአፍሪካ ሀገራት አንድም የኢንተርኔት መዘጋት አለመመዝገቡን፤ በሌሎች 14 ሀገራት ደግሞ የኢንተርኔት መዘጋት የገጠመው አንድ፣ አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን አስታውሷል።

በአህጉሪቱ የተፈጸመው የኢንተርኔት መዘጋት ክስተት በመጠንና በድግግሞሽ ብቻ ሳይሆን ለድርጊቱ መፈጸም መንስኤ በሆኑ ገፊ ምክንያቶች ጭምርም ሰፊ ልዩነት የሚታይበት መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።

የመንግሥታት ሕዝባዊ አመጽን መፍራት፣ በሀገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ግጭቶችና ጦርነቶች፥ ምርጫን ተከትለው ሊቀሰቀሱ የሚችሉ አመጾች፥ የፈተና መሰረቅንና መጭበርበርን ለማስቀረትና የፖለቲካ ተቃውሞን ለማፈን የሚወሰዱ እገዳዎች ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአህጉሪቱ ለተፈጸሙ የኢንተርኔት መዘጋትና በኢንተርኔት ነጻነት ላይ ለተፈጸሙ ገደቦች ዋነኛ መንስኤ ሆነው መለየታቸውንም ጥናቱ ገልጿል።

ኢትዮጵያን በተመለከተም የኢንተርኔት መዘጋት በተለይም በግጭትና በጦርነት ወቅት ሊኖረው የሚችለው ውጤትና በዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ በጥናቱ መካተቱን አዲስ ማለዳ በዘገባዋ አመልክታለች፡፡

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.