Logo
Getu Temesgen
ግዮን ሆይ አግሣ‼️
#ethiopia | ዓባይ መንገደኛው ወዴት ትሄዳለህ ?
እናትህን ኢትዮጵያን ለማን ትተዋለህ?
እያለ ዜመኛው...
በአራራይ በርክርክ ያንቆረቆረልህ፤
በአዲሱ ዓመት ብስራቱ ሰመረ፤
ግዮን አገሣ ዓባይ ተሞሸረ።
አምላክ ኢትዮጵያን ባረካት ወንዟንም አደላት፤
በብርቱ ልጆቿ እራት መብራት ኾናት።
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

***

ለእልፍ ዘመናት...
ስንት ሀሳብ ተነሳ ስንቱ ተረቀቀ፤
ለ14 ክረምት ስንት ወገን ወደቀ፤
ስንት ላብ ፈሰሰ ስንቱ ሀብት አለቀ፤
ስንት አየን መከራ ሰማን እንጉርጉሮ ፤
ሀሩር ከባዕድ ፊት ጠበሰን ተጣምሮ።
አሰናካዮቹ ወደታች ወረዱ በላይ አንጋጠጡ፤
በጉልበት በቁጣ ቆመው አፈጠጡ፤
በብልጠት በለቅሶ በእጅ አዙርም መጡ፤
በመረጡት ሁሉ እውነት የለምና በመጡበት ወጡ።
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

***

ሰከላ ተወልደህ ጉባ ላይ ያደግኸው፤
800 ምዕራፍ ቤትህን የዞርኸው፣
በ14 ሃምሳ በአንድ የስልክ ጥሪ፤
ትባል የነበረ የሰው ቤተ ሠሪ የሰው አኗኗሪ፤
ዓባይ ስመ ብዙ ፈለገ ዐቢይ የፈውስ ወንዝ፤
ጌዖን፣ ጊሖን፣ አባዊ ከገነት የሚመዘዝ፤
ፈፋ ቆላውን አቋርጦ ጉድጓድ ሸለቆ ሰንጥቆ፤
በበረሃ የሚጮህ በፏፏቴ ድምፁ ደምቆ፤
"ግዮን ወተት ኾኖ ገነትን ካጠጣት፤
የግዮን መነሻ ኢትዮጵያ ምንድናት?"
ቢልም ባለቅኔው መፍቻ አለው ብልኃት፤
የጥበባት መፍለቂያ የምስጢራት መገኛ፤
ኢትዮጵያ ሀገር ናት ምድረ ቀደምት የኛ።
ያገር ልጅ የማር እጅ ያባይ ልጅ ሳቢሳ፤
በጥቅሻ ተጠርቶ የስንፍናን መግነዝ በጥሶ ተነሳ፤
ምስጋና ለእናንተ ለዓባይ ወንዝ ልጆች ፤
የሙላቱን ብስራት ላሰማችሁ ጀግኖች ፤
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

***

ጃንሆይ ዘክረው ጉልበት ቢከዳቸው፤
ወረታቸው ቢጎድል ጥሪቱም ቢያጥራቸው፤
"በትውልድ ይገንባ"
የሚል ጦማር ጻፉ አደራ ፈርመው፤
እኛም ትውልድ ነን ያባት ቃል አክባሪ፤
የዘመናት ቁጭት መርገምን ሰባሪ፤
መንገድ የሳተውን በመስመሩ መሪ፤
ራዕይ ፈጻሚዎች ትልም ተላሚዎች፤
ትዕምርት የምናቆም ጡብም ደርዳሪዎች፤
ወረት ሰብሳቢዎች ጥሪት ቋጣሪዎች፤
የአባት ሕልም ፈተን ለልጅ የምናወርስ፤
በዘመን ሀዲድ ላይ የልብ የምናደርስ፤
ተደግፈን ያለምን በአበው መከዳ፤
ስብራት ጠጋኝ ነን የምፍቅ እዳ።
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

***

የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው የሚል ተረት ተሰረዘ፤
የውጪ አልጋ የውስጥ ቀጋ መርገምህ ተደለዘ፤
ወርቅ ግንዱን ይዞ አይዞርም በያገሩ፤
ልብ ገዝቶ ተመልሷል ወደ ምድሩ፤
ገባር ወንዞች በኅብር ቆመን የተጋመድን፤
ጨለማ አሳብ ረገፈ እንደችቦ ስለበራን፤
ዓባይ ምግብ መጠጥ ዓባይ ኃይል ኾነ፤
የተሠበረው ስማችን በአደባባይ ተጠገነ፤
የጎደፈው ክብራችን በዓለም ላይ ገነነ ፤
ወድቀን ተነስተናል ጀምረን ጨርሰናል ፤
ከእንግዲህ ለመብረር የቱ ያቆመናል፤
ዓባይ ዘረ ብዙ ዓባይ ስመ ብዙ፤
ተበጣጥሶ ወድቋል ሴራና መዘዙ።
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

***

የሀገሬ ልጆች የሀገሬ አፍላጋት በሉ ተደሰቱ፤
የጠፋው ልጅ ዓባይ ተመልሷል ቤቱ፤
አዲስ ልብስ አልብሱት አብሉት ከሙክቱ፤
ቀለበት አርጉለት በጌጠኛ ጣቱ፤
"ከሰው ቤት እንጀራ ከተሞናሞነው፤
የእናት ቤት ይሻላል የዋለ ያደረው፤"
የሚል ዜማ ሰምቶ ዓባይ ልብ ገዛ፤
ገብር ኄር ተባለ ፊቱ በጠል ወዛ፤
ከእንግዲህ እናትህን አገልግል ተነሳ፤
በበጎ ፈቃድህ ጎረቤት አትርሳ ፤
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

***

አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ጀጎል፣ ጢያ፤
የተጋድሎው ትዕምርት..
ከዓባይ ላይ ደረሰ ሐረግ ማስቀጠያ፤
የድል ታሪክ ብስራት በዓለም መታያ፤
ዳግማዊ አድዋ የእድገት መብቀያ፤
የአደባባይ ኩራት ጠላት በመቀያ፤
የእውነት ምስክር ሀቅ የኢትዮጵያ ፤
እባብ ጊንጥ እሾሁን እየተራመድነ፤
ይቻላል ያልነውን ችለን አሳየነ፤
በብርቱ ልጆቿ ደም ላብና ፍቅር፤
በጽኑ ተጋድሏቸው ወዝና ክብር፤
ኢትዮጵያ ሀገሬ ለዘላለም ትኑር።
ግዮን ሆይ አግሣ እንደ ጥቁር አንበሳ፤
እንደ እንግጫ ደንፋ ፈንድቅ እንደ እንቦሳ፤
እንጉርጉሮህ በቃ መርገምህ ተነሳ።

የሀብከ ብርሃኔ ጥላሁን

1 year ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.