Logo
YenetaTube
ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሙያ ፈቃድ ብቻ ሲሰሩ ለነበሩ አካላት የግብር ስሌት አሰራር ተዘረጋ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2018 የግብር ዘመን ማስታወቂያን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው አዲስ አሰራር በሙያ ፈቃድ ብቻ ሲሰሩ ለነበሩ አካላት የሚሆን የግብር ስሌት አሰራር መዘረጋቱን አስታውቋል።

አሐዱ ሬዲዮ በተመለከተው በዚህ አዲስ አሰራር መሠረት ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሙያ ፈቃድ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ጠበቆች ፣ የኢንሹራንስ ወኪሎች ፣ የኢንሹራንስ ጉዳት ገማቾች እና ሌሎች ተመሳሳይ ባለሙያዎች ይካተታሉ።

እነዚህ አካላት የሂሳብ መዝገብ የማቅረብ ሕጋዊ ግዴታ ቢኖርባቸውም፣ መዝገብ ሳያቀርቡ ሲቀሩ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት መመሪያው ግልጽ የስሌት አሰራር አስቀምጧል።

በአሰራር ስርዓቱ መሠረት በሙያ ፈቃድ ብቻ ሲሰሩ የነበሩ ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ ባላቀረቡበት ሁኔታ ከአጠቃላይ ገቢያቸው ላይ 35 በመቶው እንደ ወጪ ታስቦ ቀሪው 65 በመቶ ደግሞ ግብር የሚከፈልበት ገቢ እንደሆነ ተቆጥሮ ግብራቸው እንዲሰበሰብ ይደረጋል።

ይህ አሰራር ህጋዊ አሰራርን ለማስፈንና በሙያዊ አገልግሎቶች ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ የግብር ስወራዎችን ለመቀነስ አልሞ የተዘጋጀ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ለ2018 የግብር ዘመን ብቻ ተግባራዊ እንደሚሆን ቢሮው አመልክቷል።

እነዚህ ባለሙያዎች ወደፊት ህጋዊ የሂሳብ መዝገብ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ የማስተካከያ እርምጃዎችና የቃል መሐላ ስነ ስርዓቶች እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

አሐዱ ራዲዮ

16 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.