Logo
EBC
የካይሮ የሴራ እንቅስቃሴ እና የኢትዮጵያ የማይናወጥ የከፍታ ጉዞ
******************

የታሪክ የሉዓላዊነትና የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የሚሰነዘሩባትን ሁለገብ ተፅእኖዎችና መሰናክሎች አልፋ የብልፅግና ጉዞዋን በፅናት እያስቀጠለች ትገኛለች።

ሀገራችን ያላትን ሰፊ ለም መሬት፣ የተትረፈረፈ የውሃና የማዕድን ሀብት እንዲሁም ታላቅ የሰው ሀይል ከህዝቧ የኑሮ ደረጃ ጋር ለማጣጣምና ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በፈጣን የልማት ሂደት ላይ ትገኛለች።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት ለማጨናገፍ ከታሪካዊ ጠላቶችና ከእነሱ ጋር ከተሰለፉ የውስጥ ከዳተኞች የሚሰነዘሩት ትንኮሳዎችና የጥፋት እንቅስቃሴዎች ዛሬም የሀገራችንን ሉአላዊነት ለመሸርሸር ያለሙ መሆናቸው ይታወቃል።

የዓባይ ወንዝን ፍሰትና ፍትሃዊ ጥቅም በተመለከተ የካይሮ መንግስት የሚከተለው ፖሊሲ የኢትዮጵያን የመልማት መብት ለመገደብ ያለመና በቅኝ ግዛት ዘመን የቆዩ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ውሎች በማንሳት ላይ የተመሰረተ ነው።

እነዚህ ጠላቶች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከመጀመሪያው አንስቶ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስኮች ለማደናቀፍ የውስጥ ተላላኪዎችን በመሳሪያነት በመጠቀም ቀጠናው ሰላም እንዳያገኝ ሲጥሩ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝን በፍትሃዊ፣ ምክንያታዊና በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት በማያደርስ መርኋ መሰረት ውሃውን ለልማቷ እያዋለች ትገኛለች።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የደለል ክምችትን በመቀነስ የጎርፍ አደጋን በመከላከልና ንፁህ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካን የኃይል እጥረት የሚቀርፍና እውነተኛ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያረጋግጥ ዘመናዊ መሰረተ ልማት መሆኑ በተግባር ተረጋገጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግስት ምስረታ ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፤ እንደ ሀገር ቀድሞ አለመዘጋጀት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመገንዘብ የጣሊያን ዳግም ወረራን መለስ ብሎ መቃኘት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ያሰበችውን ታሳካለች ጠላቶቿንም አስወግዳ ጉዞዋን በፍጥነት ትቀጥላለች ሲሉ አስምረውበታል።

አክለውም ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የምትጠቀመው የሌሎችን ድርሻ ለመጋፋት ሳይሆን ህዝቧን ከጨለማ ለማውጣትና ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ለማደግ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በጠንካራና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተገነባ መከላከያ ሰራዊት በፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የከተሞች ኮሪደር ልማትና በግብርና እራስን የመቻል እንቅስቃሴ ባሉ ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች የቀጠናውን መሪነቷን አጠናክራለች።

ከአፍሪካ ሁለተኛ ባለ ብዙ ቁጥር ህዝብ ያላት ሀገር እንደመሆኗ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግና ለማረጋገጥ በታሪካዊ ስህተት ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በሰጥቶ መቀበል መርህ እውን ለማድረግ ብሄራዊ አጀንዳ አድርጋ እየሰራች ሲሆን ጥያቄውም በአለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ በማግኘት ላይ ይገኛል።

እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የባህር በር ማግኘት ለዛሬው ትውልድ የህልውናና የሁለተኛው ትውልድ የመልማት የመበልፀግና የሀገር ፍቅር ንቅናቄ ጉዳይ መሆኑ የውጭ ጫናዎችና ጂኦፖለቲካዊ ተቃውሞዎች የህዝቡን አንድነት የበለጠ የሚያጠናክሩት በመሆናቸው ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ለቀጣዩ ትውልድ የበለፀገች ሀገር የማስረከብ አርበኝነትን በተግባር መወጣት ይገባናል።

በብሌን ደምበሎ
#ethiopia #የመደመርመንግሥት #ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

16 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.