Logo
Ethio telecom
8 ፍሬያማ ዓመታት፤ ትሩፋት ላለው ሕይወት!

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክብርት ፍሬሕይወት ታምሩ በደንበኞቻችን እና በኩባንያችን ቤተሰብ አጠራር "ፍርዬ" ባለፉት ስምንት ዓመታት ባሳዩት ወደር የለሽ ጽናት፣ ብስለትና ቁርጠኛ አመራር ተቋማችን ዘመን ተሻጋሪና አመርቂ ታሪካዊ ስኬቶችን እንዲያስመዘግብ አስችለዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚያችን ከስምንት ዓመታት በፊት አንጋፋውን ኩባንያችንን ሲረከቡ፣ ተቋሙ ሰፊ መሠረተ ልማትና እምቅ አቅም ቢኖረውም ወደ ተጨባጭ ውጤት ያልተቀየረ፣ “ያንቀላፋ ግዙፍ” (The Sleeping Giant) ተብሎ የሚታወቅ፣ በከፍተኛ የዕዳ ጫና የተተበተበ፣ የታሪፍ ውድነት ቅሬታ የነበረበት እንዲሁም የአገልግሎት አማራጮቹ በ3ጂ እና በጥቂት አካባቢዎች ብቻ በ4ጂ የሞባይል ዳታ የተገደቡበት እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም ‘ኢትዮ ቴሌኮምን በመቀየር የሀገራችንን ዕድገት ማፋጠን እንችላለን’ የሚል የጋራ ራዕይ በማስረጽ፣ ሰውን ያማከለ (Human Centric) እሴትን በማስፈንና ልህቀትን (Excellence) መርህ በማድረግ መላውን ሠራተኛ በአንድ ዓላማ አሰልፈዋል። የተቀመጡትን ስትራቴጂያዊ ግቦች መላው የተቋማችን ቤተሰብ በከፍተኛ ዲሲፕሊንና ትጋት ወደ ተግባር በመቀየሩም፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ለሀገር ኩራት የሆነ ተቋም እንደገና መገንባት ተችሏል።

በዋና ሥራ አስፈጻሚያችን የላቀ አመራር መሠረታዊውን የቴሌኮም ግንኙነት (Connectivity) አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ መጠነ-ሰፊ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያና ማሻሻያ ሥራዎች፣ የደንበኞቻችን ቁጥር ከ37.9 ሚሊዮን ወደ 90.1 ሚሊዮን አድጓል፤ 99.8 በመቶ ሕዝባችን የአውታረ መረብ (Network) ሽፋን ሲያገኝ ደንበኛ የመሸከም አቅማችን 115.1 ሚሊዮን ደርሷል። የ4ጂ የሕዝብ ሽፋናችን ከ82.2 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ሀገራችን ዘመናዊውን የ5ጂ ቴክኖሎጂ ቀድመው ተግባራዊ ካደረጉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ በማድረግ ዛሬ አገልግሎቱ በ33 ከተሞች ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል።

በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ በተወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎች የኩባንያችን ዓመታዊ ገቢ ከ37.16 ቢሊዮን ብር ወደ 215.8 ቢሊዮን ብር፣ ከወለድና ከታክስ በፊት ያለው ትርፍ (EBITDA) ከ14.9 ቢሊዮን ብር ወደ 92.99 ቢሊዮን ብር አድጓል። በተጨማሪም በአቅራቢዎች የፋይናንስ ድጋፍ (Vendor Financing) ለተገነቡ መሠረተ ልማቶች የተወሰደው 1.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ ተጠናቋል።

በዋና ሥራ አስፈጻሚያችን ሃሳብ አመንጪነት የሀገራችን ፈር ቀዳጅ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት የሆነውን “ቴሌብር”ን እውን በማድረግ፣ የክፍያ ሥርዓቱን ከማዘመን ባለፈ ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማረጋገጥ ባሻገር አጠቃላይ የዲጂታል ሥነምህዳሩን ለማነቃቃት ተችሏል። ያለማስያዣ የሚሰጡ የብድር አገልግሎቶችን፣ የቁጠባ ባህልንና አጠቃላይ የዲጂታል ግብይትን ወደ ማኅበረሰቡ በማስረጽ፣ ቴሌብር ዛሬ ከ60 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ምርጫ በመሆን ከ9.13 ትሪሊዮን ብር በላይ ግብይት ማስተናገድ ችሏል።

ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉት ዘመኑን የዋጁ ሦስት ስትራቴጂዎች ኩባንያችንን ከመሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢነት ወደ የተቀናጀ የዲጂታል መፍትሔዎች መሪነት አሸጋግረውታል። የዳታ ማዕከልና የቴሌክላውድ አገልግሎቶች፣ ዘኔክሰስ፣ ቴሌስትሪም፣ ዘመን ገበያ እንዲሁም የፋይበር መስመር ዝርጋታና የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቮች በማከናወን የማኅበረሰቡን አኗኗር በማቅለል፣ የመንግሥት ተቋማትን አሠራር በማዘመንና የንግድ እንቅስቃሴን በማቀላጠፍ የሀገራችንን ዲጂታል ራዕይ ዕውን የማድረግ ሂደትን በግንባር ቀደምትነት መርተዋል።

በክብርት ዋና ሥራ አስፈጻሚያችን ፍሬሕይወት ታምሩ አመራር ተነድፎ በመተግበር ላይ የሚገኘው “ቀጣዩ አድማስ፡ ዲጂታልና ከዚያም ባሻገር 2028” (Next Horizon: Digital and Beyond 2028) ስትራቴጂ የሀገራችንን የልማት አቅጣጫና የዘርፉን የወደፊት ዕድሎች ያገናዘበ ነው።

ለተቋማችን ታላቅ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መሳካት ጉልህ አሻራ ያሳረፉት፣ በኢትዮ ቴሌኮም ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዋና ሥራ አስፈጻሚና ለመላው የሀገራችን ሴቶች የጥንካሬ ተምሳሌት የሆኑት ክብርት ፍሬሕይወት ታምሩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የተሰማንን ልባዊ ደስታ እየገለጽን፣ በቀጣዩ የሥራ ዘመናቸው የላቀ ውጤትና ስኬት እንዲጎናጸፉ ከልብ እንመኛለን።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ፍሬሕይወት ታምሩ በተቋማችን ውስጥ ባሳዩን ፍቅር፣ የማይናወጥ ጥንካሬና የቁርጠኝነት ተምሳሌትነት ምንጊዜም በልባችን በከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር የሚኖሩ ሲሆን፤ መላው የተቋማችን ቤተሰብ እርሳቸው የጣሉብንን አደራ በጽናት ይዞ ይቀጥላል።

በዚህም የ'ቀጣዩ አድማስ' ስትራቴጂን ከዳር በማድረስ፣ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችና የሚቀርቡ ዲጂታል መፍትሔዎች ለሕዝባችን ተጨባጭ ፋይዳ እንዲሰጡ በማድረግ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማፋጠን ዋና ሥራ አስፈጻሚያችን ክብርት ፍሬሕይወት ታምሩ ሁሌም የሚኮሩብን ታታሪ ቤተሰብ ሆነን እንዘልቃለን።

8 hours ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.