Logo
YenetaTube
«በሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት መስደዱ ሊበቃ ይገባል» — የወሎ ራያ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ

የራያ ስድስቱ ወረዳዎች ጊዜያዊ አስተዳደር የማዋቀር ሂደት ሌላ ግጭትና ጦርነት ከመጋበዙ በፊት በአስቸኳይ እንዲቆም ተጠየቀ።

በራያ ስድስቱ ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር የማዋቀር ሂደት ገለልተኛ አለመሆኑን እና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ መሆኑን በመጥቀስ ሂደቱ ወዲያውኑ እንዲቆም የወሎ ራያ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።

ኮሚቴው ዛሬ ባወጣው መግለጫ የራያ ህዝብ ማንነትና ወሰን ጥያቄ ሕጋዊ፣ ሰላማዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ እልባት ከማግኘቱ በፊት፣ አንድን ወገን ብቻ በሚጠቅም አካሄድ የሚዋቀር ጊዜያዊ አስተዳደር ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።

የአካባቢው ችግርም በሕግ፣ በማስረጃ፣ በሕዝብ ተሳትፎ እና በሕዝበ-ውሳኔ ብቻ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚገባ አስገንዝቧል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ማዋቀር ሂደት ላይ የተነሱ ዋና ዋና ቅሬታዎች፦

ሂደቱን እየመሩ ያሉት አካላት ከፌዴራል መንግሥት ተልእኮ እንደተሰጣቸው ቢገልጹም፣ በይፋ የቀረበ የሥልጣን ሰነድ ወይም ደብዳቤ አለመኖሩ አጠያያቂ አድርጎታል

በራያ አላማጣ እየተካሄደ ባለው ሂደት የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ተፈናቃዮች በቂ ውክልና አላገኙም።

ሂደቱ በስምረት ፓርቲ እና በትግራይ ሰላም ኃይል (TPF) አመራሮች ብቻ የሚመራ በመሆኑ የገለልተኝነት ጥያቄ አስነስቷል።

በ2018 ዓ.ም. የተፈናቀሉ ዜጎች በደህንነትና በክብር ወደ ቀድሞ ቀያቸው ባልተመለሱበት ሁኔታ አስተዳደር ለማዋቀር መቸኮል ተጨማሪ ስጋት ይፈጥራል።

ታጣቂዎች ትጥቅ ባላስረከቡበት፣ እንዲሁም መስከረም 23 ቀን 2019 ዓ.ም. በሰላማዊ ዜጎች እና በራያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በገለልተኛ አካል ሳይጣሩ የሚደረግ አደረጃጀት ተቀባይነት የለውም።

የፕሪቶሪያ ስምምነት እና የመከላከያ ሰራዊት ሚና መግለጫው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ የአካባቢውን ሰላምና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት አድንቆ፤ የአስተዳደር ማዋቀር ሂደቱ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መንፈስ እና ከሀገራዊ ምክክር መርሆዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ብቻ መመራት እንዳበት አሳስቧል።

በማጠቃለያም መንግሥት የጊዜያዊ አስተዳደር ማዋቀሩን አቅጣጫ በይፋ እንዲያብራራ እና የራያ ሕዝብ መብት በሚያስከብር መንገድ ሂደቱን እንዲያስተካክል ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.