Logo
FBC
ኢትዮጵያ ታከብራችኋለች!

የሀገር ህልውና፣ ክብር እና ልዕልና የሚለካው በድንበሮቿ ፅናት እና በህዝቦቿ ሰላም ነው።

ይህንን ሰላም እና ክብር ደግሞ ሌሊት ከቀን፣ በደምና በአጥንታቸው እየገነቡት ያሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው። ታሪክ ይለወጣል፣ ትውልድ ያልፋል ነገር ግን ሀገርን ለማፅናት የተከፈለ መስዋዕትነት ሁልጊዜም በክብር መዝገብ ላይ በደማቅ ቀለም ተፅፎ ይኖራል።

ኢትዮጵያ ዛሬም ኩሩ እና ሉዓላዊት ሀገር ሆና እንድትቀጥል ያደረገው የሠራዊቷ የማይበገር ፅናት ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ጠላቶች አከርካሪያቸውን እየሰበረ፣ ዳር ድንበሯን በደሙ እና በአጥንቱ እየጠበቀ ዛሬም በልበ ሙሉነት ቀጥሏል።

የሀገሪቱን አንድነት ለመናድ እና ህልውናዋን አደጋ ላይ ለመጣል የሚነሱ ማናቸውንም የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ሴራ በማክሸፍ ረገድ የሠራዊቱ ሚና ወደር የለውም።

ይህ ሠራዊት የሰላም ዘብ ብቻ አይደለም፤ የሀገር ሉዓላዊነት የመጨረሻው ምሽግ እና የኩራት ምልክት እንጂ።

የዚህ ሠራዊት ክንዱ ብረት ያቀልጣል! ተራሮችን የሚያናውጥ፣ ጋሬጣዎችን የሚጠርግ እና ማንኛውንም የጠላት ምሽግ የሚያፈራርስ ወታደራዊ የአሸናፊነት ወኔ የተላበሰ ነው።

በጥበብ፣ በብስለት እና በከፍተኛ ሥነ ምግባር የታነፀው መከላከያ ሠራዊታችን የጥፋት ኃይልን ሁሉ ድባቅ በመምታት ሁልጊዜም ድልን ለሀገሩ ያበስራል። ይህ የጀግንነት ሥነ ልቦና እና በላቀ ወታደራዊ ሳይንስ የተገነባው አቅም ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትቆም አድርጓታል።

ሰሞኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ መክፈቻ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር የሠራዊቱን ድንቅ ተጋድሎ በኩራት አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ “የመከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ አካላት ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የመታደግ እና በክብር የማቆየት ትጋታቸው በዘመናት የሚዘከር ነው” በማለት የላቀ እውቅና ሰጥተዋል።

አክለውም ለሠራዊቱ አባላት ያላቸውን ክብር ሲገልጹ÷ “ለቆራጥነታችሁ፣ ለሀገር ፍቅራችሁ፣ ለመፈጸም ብቃታችሁና ለህዝብ ወዳጅነታችሁ መንግስት የላቀ አክብሮት አለው” በማለት የሠራዊቱን የሀገር ፍቅር ጽናት መስክረዋል።

ይህ የሀገሪቱ የበላይ መሪ ምስክርነት ሠራዊቱ የሀገር ጋሻ እና የህዝብ ኩራት መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠ ነው።

ስለሆነም ህይወታችሁን ለህዝብ ሰላምና ለሀገር አንድነት አሳልፋችሁ የሰጣችሁ፣ በየበረሃውና በየሰንሰለታማ ተራሮች ላይ በብርድና በሙቀት ሀገራችሁን የምትጠብቁ የሠራዊቱ አባላት በሙሉ ታሪክ አይረሳችሁም፣ ትውልድም ያመሰግናችኋል።

ኢትዮጵያ በጀግንነታችሁ ትኮራለች ፤ ኢትዮጵያ ታከብራችኋለች!

በኃይለኢየሱስ መኮንን

2 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.