Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የዩናይትድ ስቴትስ የኮንግረስ አባል ያሳሚን አንሳሪ በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ዳግም አገርሽቷል ባሉት የእርስ በርስ ጦርነት እጅግ ማዘናቸውን እና መጨነቃቸውን አስታወቁ።
የኮንግረስ አባሏ በይፋዊ የኤክስገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ነገር ግን ጥብቅ መልዕክት፣ ተፋላሚ ኃይሎች በአስቸኳይ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

"በኢትዮጵያ ዳግም ባገረሸው የእርስ በርስ ጦርነት እጅግ ተጨንቄያለሁ፣" ያሉት ኮንግረስ ውመን ያሳሚን፣ "በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ጭካኔ እና መከራ ባስተናገዱባት ትግራይ፣ ግጭቱ በድርድር ወደሚገኝ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲመለስ አጥብቀን ልንጠይቅ እና ጫና ልናደርግ ይገባል" ብለዋል።

አክለውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጥ እንደማይችል በማስጠንቀቅ፣ "ይህ አውዳሚ ብጥብጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ዜጎችን ህይወት እንዲቀጥፍ መፍቀድ የለብንም" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኮንግረስ አባሏ ይህንን መግለጫ ያወጡት ባለፉት ሳምንታት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ አካባቢዎች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አዳዲስ የተኩስ ልውውጦች መከሰታቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ባለበት ወቅት ነው። የያሳሚን አንሳሪ አስተያየት፣ የአሜሪካ መንግስት እና ህግ አውጪዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ዳግም ዲፕሎማሲያዊ ትኩረት መስጠት መጀመራቸውን የሚያመላክት ነው።

1 day ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.