Logo
YenetaTube
አንጋፋው ድምፃዊ ግርማ ነጋሽ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

በኢትዮጵያ ወርቃማው የሙዚቃ ዘመን ከ60 በላይ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራዎችን ያበረከተው አንጋፋው ድምፃዊ ግርማ ነጋሽ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ከአንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ጋር በነበረው የሰፈር ልጅነት ቅርበት ወደ ጥበቡ ዓለም የገባው ግርማ ነጋሽ፣ መጀመሪያ በፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ በኋላም በብሔራዊ ቲያትር ቤት በድምፃዊነት በማገልገል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የራሱን ደማቅ አሻራ አኑሯል።

ከ60 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትና እስከዛሬ ድረስ በአድማጮች ዘንድ የሚወደዱት “የኔ ሐሳብ” እና “ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ” የተሰኙት ሥራዎቹ የመድረክ ላይ አምባሳደሮቹ ነበሩ።እ.ኤ.አ. በ2011 በአዲስ አበባ ከታዋቂው Either/Orchestra የጃዝ ባንድ ጋር በመሆን “የኔ ሐሳብ” የተሰኘውን ታሪካዊ ሥራውን በጃዝ አቀራረብ ዳግም መድረክ ላይ በማቅረብ አዲስ ትውልድ አገናኝቷል።በጥበብ ዘመኑ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽዖም በሰሜን አሜሪካ የሙዚቀኞች ማኅበር አማካይነት የሕይወት ዘመን የክብር ሽልማት ተበርክቶለታል።

የሦስት ወንዶችና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበረው የአንጋፋው ድምፃዊ ግርማ ነጋሽ የቀብር ሥነ-ሥርዓት፣ ነገ መስከረም 14/2019 ዓ/ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።

17 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.