Logo
SeledaPost
የጓደኛውን የባንክ ደብተር የሂሳብ ቁጥር በመውሰድ 20ሺህ ብር ያወጣው ግለሰብ ክስ ተመሰረተበት።

ግለሰቡ ወንጀሉን የፈጸመው ጳጉሜ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከጥዋቱ 3:00 ሰዓት በንፍስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ከሚገኝ ባንክ ውስጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ጉታ ገመዳ የተባለው ግለሰብ ከግል ተበዳይ ጋር በጓደኝነት አንድ ቤት ውስጥ የሚኖር ሲሆን፤ የግል ተበዳይ ቤት ውስጥ ያስቀመጠውን የባንክ ደብተር የሂሳብ ቁጥሩን በመውሰድ ከግል ተበዳይ የሂሳብ ደብተር ፊርማ ጋር በማመሳሰል በክ/ከተማው ወረዳ 7 ከሚገኝ ባንክ 20ሺህ ብር ወጪ አድርጓል፡፡

ግለሰቡ ገንዘቡን ካወጣ በኋላ የግል ተበዳይ በደረሰው መልዕክት አማካኝነት ባንኩን በመሄድ ይጠይቃል።ገንዘቡ  ወጪ መደረጉን ምላሽ የተሰጠው የግል ተበዳይ ጉዳዩን ለአቅራቢያው ሙገር ፖሊስ መምሪያ አመልክቷል፡፡

አቤቱታው የደረሰው ፖሊስም ምርመራውን በማጣራትና ባንኩ ውስጥ የነበረን ካሜራ በመጠቀም ወንጀል ፈጻሚውን በመለየት ከነ ኤግዚቢቱ ማስመለሱን የመምሪያው የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ ኃላፊ ኢ/ር ዮሴፍ ገረመው ተናግረዋል።

ወንጀል ፈጻሚው ክስ እንደተመሰረተበትም ኃላፊው ገልፀዋል።

ግለሰቦች የባንክ ደብተር የሂሳብ ቁጥራቸውን ከራሳቸው ውጪ ለየትኛውም አካል አሳልፈው መስጠት ወይም በግዴለሽነት ለወንጀል ተጋላጭ በሆነ ቦታ ማስቀመጥ እንደሌለባቸው የገለጹት ኃላፊው ደንበኞች ገንዘብ ለማውጣት ወደ ባንክ ሲሄዱም የባንክ ባለሙያዎች የሂሳብ ደብተሩ ባለቤት ትክክለኛ ማንነቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Seledadotio
Seledadotio
18 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.