Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በቅርቡ በአማራ ፋ*ኖ* ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋ*ብን) እና በሌሎች ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተፈረመውን አዲስ ጥምረት (ትብብር) አጥብቀው የሚቃወሙት ታዋቂው ፖለቲከኛ እና የአፋብን አባል እስክንድር ነጋ፣ ስምምነቱ የአባላትን እውቅና እና ህጋዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን የጣሰ መሆኑን በማጋለጥ ለድርጅቱ ፖሊት ቢሮ እና ለህዝብ ግልጽ ደብዳቤ አሰራጩ።

መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) በተጻፈው እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በወጣው ሰፊ መግለጫቸው፣ እስክንድር ነጋ በአፋ*ብን አመራሮች (በተለይም በአርበኛ ዘመነ ካሴ) እና በሌሎች ቡድኖች መካከል የተደረገውን ይህን የትብብር ስምምነት "በአማራ የህልውና ትግል ላይ የተፈጸመ ታላቅ በደል" ሲሉ ኮንነውታል።

እስክንድር ነጋ በደብዳቤያቸው እንዳብራሩት፤ አፋብን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ህዝባዊ ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም፣ የአመራር ብቃት ማነስ እና የህግ የበላይነት መጥፋት ድርጅቱን እየጎዳው ይገኛል። አዲሱ ጥምረትም ቢሆን፣ አብዛኛው የአፋብን አባል እና አመራር በማያውቀው ሁኔታ በድብቅ ሲካሄድ ቆይቶ በመጨረሻ በአርበኛ ዘመነ ካሴ አማካኝነት በሚዲያ መነገሩን እስክንድር ተችተዋል።

ተቃውሟቸው ያነጣጠረው በስምምነቱ ሂደት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ አብረው ከተሰለፉት ኃይሎች የጀርባ ታሪክም ላይ ጭምር ነው። በደብዳቤያቸው ላይ እንደገለጹት፣ ከአፋ*ብን ጋር የትብብር ስምምነት አድርገዋል የተባሉት ህወሓት፣ ኦነ*ግ/ሸ*ኔ እና የጉምዝ ነ*ጻ አውጪ ቡድኖች፣ ጸ*ረ-አማራ እና ጸ*ረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ የፈጸሙ እና በዓለም አቀፍ ተቋማት የተረጋገጠ የሞራል እና የህግ ተጠያቂነት ያለባቸው ናቸው። ከእንደዚህ አይነት ኃይሎች ጋር የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት፣ መጀመሪያ ለፋኖ ሰራዊት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት የብዙሃኑን ድጋፍ ማግኘት እንደነበረበት እስክንድር አሳስበዋል።

የአፋ*ብን የአሁኑ አመራር በጉባኤ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ያልተመረጠና የፋኖን አንድነት ለማምጣት በጊዜያዊነት የተቀመጠ በመሆኑ፣ ይህን መሰል ትልቅ ታሪካዊ ውሳኔ ለማሳለፍ ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ ስልጣን እንደሌለው እስክንድር በደብዳቤያቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል።

እነዚህን ህጋዊ ጥያቄዎች በማንሳታቸው እና ለጀርመን ድምጽ ሬድዮ መግለጫ በመስጠታቸው ምክንያት፣ የአፋ*ብን ፖሊት ቢሮ እሳቸውን ለማሳሰር ትዕዛዝ ማስተላለፉን ያጋለጡት እስክንድር፣ ሆኖም የበታች መዋቅሩ ትዕዛዙን ባለመቀበል የህግ የበላይነት እንዲከበር ማሳየቱን ገልጸዋል። በመጨረሻም "ያለ አባላት ተሳትፎ የተቋቋመው ጥምረት በአሸዋ ላይ እንደቆመ ቤት ወጀብን መቋቋም የማይችል ነው" ያሉት እስክንድር ነጋ፣ የፋ*ኖ አባላት መብት እና የህግ የበላይነት እስኪረጋገጥ ድረስ እስርም ሆነ ግድያ ሳያስፈራቸው ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

18 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.