Logo
Getu Temesgen
ጋዜ ማስቃላ እና ዮኦ ማስቃላ፤
የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የአንድነትና የባህል መገለጫ

ሳውላ፣ ጎፋ — ደቡብ ኢትዮጵያ
#ethiopia | በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን የሚገኙት የጎፋና የኦይዳ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት የሆኑትን “ጋዜ ማስቃላ” እና “ዮኦ ማስቃላ” በየዓመቱ በልዩ ድምቀት ያከብራሉ። በ2019 ዓ.ም. የሚከበሩት በዓላትም በመስከረም 13 እና 14 ቀን በሳውላ ከተማ ይከበራሉ።

ጋዜ ማስቃላና ዮኦ ማስቃላ አዲስ ዘመንን ከመቀበል ባሻገር፣ የጎፋና የኦይዳ ሕዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና የአብሮነት እሴቶች የሚያንጸባርቁ ሕያው ባህላዊ በዓላት ናቸው።

በዓላቱ የቤተሰብና የጎረቤት መሰባሰብ፣ የጋራ ማዕድ፣ መረዳዳትና መተሳሰብ በተግባር የሚገለጹበት ወቅት ነው። በተለይም በዓሉ በተጣሉ ሰዎች መካከል ዕርቅ የሚፈጠርበት፣ የተኮራረፉ የሚቀራረቡበት፣ ቂምና በቀል በይቅርታና በመግባባት የሚተካበት የማኅበረሰብ የእርቅ መድረክ መሆኑ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል።

በበዓሉ ወቅት ሽማግሌዎች ለትውልዱ ምርቃትና የሕይወት ምክር ይሰጣሉ። የአባቶች ዕውቀትና ልምድ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍበትም ልዩ መድረክ ይፈጠራል።

የደመራ ሥነ-ሥርዓት፣ የባህላዊ ዜማና ጭፈራ፣ የባህላዊ አልባሳት ውበት፣ የምስጋናና የምርቃት ሥነ-ሥርዓቶችም የበዓሉን ድምቀት ይጨምራሉ። የባህል ሥነ-ሥርዓቶቹ የሁለቱን ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስርና የባህል ሀብት በግልጽ ያሳያሉ።

እነዚህ በዓላት የዘመን መለወጫ ሥነ-ሥርዓት ብቻ ሳይሆኑ፣ የሕዝቦችን የመከባበር፣ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴቶች የሚያድሱ ባህላዊ መድረኮች ናቸው። ከዚህ አንጻር ጋዜ ማስቃላና ዮኦ ማስቃላ የጎፋና የኦይዳ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ የባህል ብዝሃነት አካል የሆኑ ውድ ባህላዊ ቅርሶች ናቸው።

የመስከረም ወርም በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ በርካታ ሕዝቦች የዘመን መለወጫ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት ነው። የወላይታ ጊፋታ፣ የጋሞ ዮ ማስቃላ፣ የጎፋ ጋዜ ማስቃላ፣ የኦይዳ ዮኦ ማስቃላና የጌዴኦ ዳራሮ ከእነዚህ ባህላዊ በዓላት መካከል ይጠቀሳሉ።

የእነዚህ በዓላት ዋነኛ መልዕክት የአዲስ ዘመን ተስፋን መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ያለፈውን በይቅርታ መዝጋት፣ በአዲሱ ዘመን በፍቅርና በመግባባት አብሮ ለመጓዝ ቃል መግባት ነው።

በዚህም ጋዜ ማስቃላና ዮኦ ማስቃላ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የዕርቅ፣ የአንድነትና የባህል መገለጫዎች ሆነው ይቀጥላሉ።

ዮ ጎፋ ጋዜ ማስቃላ!
ዮ ኦይዳ ዮኦ ማስቃላ!
ዮዮ ማስቃላ፣
ዳናው ዳና፣
አልባ ዙማዳ ዳና፣
ኪንቲ ሻላዳ ዳና፣
ገላኦይ ገሊውራናው ዳና፣
ሀረይ ካጨ ከሳናው ዳና፣
ዮ… ዮዮ… ዮ ማስቃላይ!

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.