Logo
Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ ዜና) የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ከአሜሪካው የማዕከላዊ ስለላ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ራትክሊፍ ጋር እሁድ ዕለት በካይሮ ተገናኝተው በጋዛ የተኩስ አቁም፣ በኢራን፣ በሱዳን እና በሶማሊያ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናው የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።

የግብጹ የደህንነት ኃላፊ ሀሰን ረሻድ በተገኙበት በዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ፣ ፕሬዚዳንት ሲሲ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚደገፈው የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል። አያይዘውም የንጹሃንን ደህንነት መጠበቅ፣ ያልተቋረጠ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና የእስራኤል-ፍልስጤምን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት የሁለት ሀገር መፍትሔ አስፈላጊነትን አስምረውበታል።

በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተደረገው ውይይት፣ ፕሬዚዳንቱ ከኢራን ጋር ያለውን የፖለቲካ ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን፤ የሱዳን እና የሶማሊያን የሀገር ሉዓላዊነት ማክበር እና ማስከበር ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል።

የሲአይኤው ዳይሬክተር ራትክሊፍ በበኩላቸው፣ ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተላከውን የሰላምታ መልእክት ለፕሬዚዳንት ሲሲ አድርሰዋል። ዳይሬክተሩ ግብጽ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት እየተጫወተች ያለውን የዲፕሎማሲ ሚና ያደነቁ ሲሆን፣ አሜሪካ እና ግብጽ በጸረ-ሽብርተኝነት እና በባህር ላይ ደህንነት (Maritime security) ጥበቃ ዙሪያ ያላቸውን ጠንካራ የሁለትዮሽ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

20 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.