Logo
SeledaPost
በሳዑዲ አረቢያ የሥራ ስምሪት ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች "መሠረተ ቢስ ናቸው" አለ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር‼️

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል ስላለው የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ሂደት ዙሪያ የሚሰራጩ መረጃዎች መሠረተ ቢስ እና ከእውነት የራቁ ናቸው ሲል አስተባበለ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራሪያ፤ “አንድም ሰው ወደ ሳዑዲ አረቢያ መሄድ አልቻለም”፣ “የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ (E-LMIS) ተዘግቷል” እና “ለኤጀንሲዎች በበቂ ሁኔታ መረጃ አልተሰጣቸውም” በሚል የሚሰራጩ ዘገባዎች የህዝብ ብዥታ የሚፈጥሩ አሉባልታዎች መሆናቸውን ገልጻል።

እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፣ የሀገሪቱ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ሥርዓት የተዘረጋው ሕጋዊ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ክብር ያለው የሥራ ዕድል ለዜጎች ለማረጋገጥ ነው። በዚህ ሂደትም ሳዑዲ አረቢያ ቁልፍ አጋር ሀገር ሆና የምትቀጥል ሲሆን፣ ፈቃድ ያላቸው የቅጥር ኤጀንሲዎችም የምህዳሩ የማይነጠል አካል ሆነው እየሰሩ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።

በሂደቱ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደባቸው እንደሚገኝ የጠቆመው መግለጫው፤ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ (E-LMIS) ሳይቋረጥ ሕጋዊ የሥራ ስምሪቱን እያቀላጠፈ እንደሚገኝ አረጋግጧል።

በመጨረሻም ሚኒስቴሩ ህዝቡ በእንደዚህ አይነት ከእውነት የራቁ መረጃዎች እንዳይደናገር እያሳሰበ፣ አሳሳች መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። ዜጎችና ባለድርሻ አካላት መረጃዎችን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይፋዊ የመረጃ መረቦች ብቻ እንዲከታተሉም ጥሪ አቅርቧል።

Seledadotio
Seledadotio
22 days ago

No replys yet!

Be the first to share what you think — your comment will appear here.